ነገረ-ኢትዮጵያ፡- ከሁለት ወር በፊት ወደ አሜሪካና የአውሮፓ አገራት ለስራ ጉብኝት ሄደው ነበር፡፡ አሁንም ወደ አሜሪካ ጉዞ ሊያደርጉ እንደሆነ ሰምቻለሁ፡፡ የአሁኑ ጉዞ አላማ ምንድን ነው?

ኢ/ር ይልቃል ጌትነት፣ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር
ኢንጅነር ይልቃል፡- መጀመሪያ ያደረኩት ጉዞ የሰማያዊ ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች የፓርቲውን አላማና ፕሮግራም፣ የሰራናቸውን እንዲሁም ወደፊት ልንሰራቸው ያሰብናቸውን ስራዎች፤ ሰማያዊ እንደ አዲስ ኃይል ሲመጣ የቆመላቸው ሀሳቦችና እምነቶች ምን እንደሆኑ ለማስተዋወቅ ታስቦ የተደረገ ነበር፡፡ የአሁኑ ግን ከበፊቱ የተለየና ለሰማያዊ ሊቀመንበር በሚል በቀጥታ በአሜሪካ መንግስት ስቴት ዲፓርትመንት የተደረገ ግብዣ ነው፡ ፡ የአሁኑ ወጣት የአፍሪካ መሪና ወደፊትም ለአገራቸው መሪ ሊሆኑ የሚችሉ፣ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ጥሩ ስራ የሰሩ፣ በውድድር ከተመረጡ በኋላ በአሜሪካ መንግስት ስቴት ዲፓርትመንት በሚደረግ ምርጫ መመዘኛዎቹን ለሚያሟሉ ሰዎች የሚሰጥ እድል ነው፡፡ በመመዘኛዎቹ መሰረት በማሸነፌ የአሜሪካ መንግስት ሙሉውን ወጭ ሸፍኖ ለሶስት ሳምንት በአሜሪካ የመንግስት አወቃቀርና ዴሞክራሲን ጨምሮ በተግባር የሚሰጡ ስልጠናዎችን የማግኘትና፣ የአሜሪካ መንግስት ባለስልጣናትም ባሉበት ከተለያዩ ተቋማት ጋርም ለመገናኘት እድል ይኖረኛል፡፡
ነገረ-ኢትዮጵያ፡- ከሌሎች የአፍሪካ አገራት የፖለቲካ መሪዎች ጋር ተወዳድረው ነው ያሸነፉት ማለት ነው?
ኢንጅነር ይልቃል፡- አዎ! ግን ሌሎች ያሸነፉ ተጨማሪ ሰዎች ይኑሩ አይኑሩ አላውቅም፡፡ ይህ የፕሬዝዳንቱም ‹ኢኒሸቲቭ› ይመስለኛል፡፡ ለእኔ ግን የተሰጠኝ አዲስ ትውልድ አመራሮች፣ ወደፊትም በአገራቸው መሪ መሆን የሚችሉ፣ ስትራቴጅካሊ የሚያስቡ፣ በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይም ሆነው መልካም ስራ ለሰሩ ሰዎች የሚሰጥ ልዩ የጉብኝት እድል ነው፡፡ በአጠቃላይ ውድድርም ተደርጎ የሚወሰድ ነው ማለት ይቻላል፡፡
ነገረ-ኢትዮጵያ፡- የአሜሪካ መንግስት ይህንን እድል ሲሰጥ እርስዎ እንደ መሪም ሆነ ሰማያዊ እንደ ፓርቲ ያሸነፋችሁበትን ዋና ዋና መመዘኛዎች ነግረዋችኋል?
ኢንጅነር ይልቃል፡- ሲመርጡኝ ዝርዝር መረጃዎችን ወስደዋል፡ ፡ መሰረታዊ የሚባሉትን ለምሳሌ ያህል የፖለቲካ ቆይታዬ፣ የትምህርት ዝግጅቴን፣ በፖለቲካው ውስጥ የነበረኝን ተሳትፎ የመሳሰሉትን መረጃዎች ለእጩነት በቀረብኩበት ወቅት ከእኔ ወስደዋል፡፡ ከዛ በኋላ ያስመረጠኝን ዝርዝር መስፈርት አላውቅም፡፡ ነገር ግን ወጣት (እስከ 45 አመት ባለው ውስጥ)፣ በአስቸጋሪ ሁኔታ መልካም ስራ የሰራ፣ ወደፊትም የአገሩ መሪ ሊሆን የሚችል የሚሉት ዋና ዋና መመዘኛዎች እንደሆኑ አውቃለሁ፡ ፡ ይህም በተለይ ከሰማያዊ አንጻር ከሁለት ነገሮች አኳያ እንድናየው ያደርጋል፡፡ አንደኛው በምስራቅ አፍሪካ ያለውን ፖለቲካና እስካሁን ጠቅልሎ የያዘው ኢህአዴግ ነበር፡፡ ሌላ አማራጭ እንደሌለ አድርጎ ነበር የሚያየው፡፡ ሆኖም እንደዚህ አይነት እድል እንደ አሜሪካ ባለ ትልቅ መንግስት የተቃዋሚ መሪ የተለየ ስራ ሰርቷል ተብሎ ሲጋበዝ ሰማያዊ ፓርቲ አዲሱንና ወደ ፖለቲካ ያልመጣውን ትውልድ ወደ ፖለቲካው ለማምጣት በሚያደርገው ጥረት እንደ አንድ ማበረታቻ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ይህ በሌሎች መስኮች ከምናደርጋቸው የዲፕሎማሲ ስራዎች በተጨማሪ ለሰማያዊ ፓርቲ ከሌሎች ፓርቲዎች በተለየ ይህኛው ግብዣ ሲደረግለት ለሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡
ከአሁን በፊት ለሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር በአሜሪካ ኤምባሲ ውስጥ የ35 አገራት ኤምባሲዎች የ‹ኢትዮጵያ ፓርትነርስ ግሩፕ› የሚባለው ሲደረግ በአመታዊ ስብሰባቸው ላይ ዋና ተናጋሪ ሆኜ ስለ ኢትዮጵያ ፖለቲካና ስለ ሰማያዊ ፓርቲ ዋና የትግል እንቅስቃሴና የወደፊት አላማችን እንዳስረዳ የተለየ እድል ተሰጥቶኛል፡፡ ይህም ለፓርቲው ሌት ተቀን ለሚሰሩ ወጣቶች፣ እንዲሁም ሁል ጊዜም ቢሆን ወጣቱ ተከታይና ጀሌ እግረኛ ከመሆን አልፎ ራሱ ኃላፊነት የሚወስድ፣ መምራትና የራሱን መሪዎች ማውጣት የሚችል ትውልድ መምጣቱን የሚያሳይ መልካም ጅምር ነው፡፡
ነገረ-ኢትዮጵያ፡- የአሜሪካ መንግስት ከ9/11 እንዲሁም ከ1997 ዓ.ም ምርጫ በኋላ ሶማሊያ ውስጥ ባለው ጥቅም ኢህአዴግ ላይ እስከመጨረሻ ግፊት ማድረግ አልቻለም ነበር፡፡ አሁን ለእርስዎና ለፓርቲዎ ይህን እድል ሲሰጥ ለኢህአዴግ የሚያስተላልፈው መልዕክት ምንድን ነው? የተቃውሞ ጎራውም ቢሆን እስካሁን የሚመራው በ1960ዎቹ ፖለቲከኞች ነው፡፡ አሁን የአሜሪካ መንግስት ይህን እድል ለእርስዎ እንደ መሪና ለሰማያዊ እንደ ወጣት ፓርቲ ሲሰጥ ለኢትዮጵያ ፖለቲካ የሚኖረው አንድምታ ምንድን ነው?
ኢንጅነር ይልቃል፡- እንግዲህ ይህን ጉዳይ ህዝቡም ሆነ የዓለም አቀፍ የፖለቲካ ማህበረሰቡ እየተረዳው የመጣ ይመስለኛል፡፡ ባለፈው አርባ አመት በገዥውም ሆነ በተቃዋሚው ያለው በአንድ አይነት እድሜና የግራ ርዕዮት የሚሽከረከር ነበር፡፡ ይህም የኢትዮጵያን ፖለቲካም ሆነ ኢትዮጵያን በሁሉም መመዘኛዎች ወደ ፊት ሊያራምድ አልቻለም፡፡ እንዲያውም ጥላቻ፣ ቂምና ቆርሾ፣ የእስር በእርስ መጠላፍና የዜሮ ድምር ፖለቲካ ሆኖ ቆይቷል፡ ፡ ያ ትውልድ ያላመጣውን ውጤትም ወጣቱ ያመጣዋል የሚል ነው፡ ፡ ኢትዮጵያ የወጣት አገር ነች፡፡ 70 ከመቶ የሚሆነው ከ35 አመት በታች ነው፡፡ ይህ የህብረተሰብ ክፍል በውክልና ደረጃም ሆነ አዲስ አስተሳሰብና ከበድ ያለ ነገር ይፈልጋል፣ ከዓለም ከተለያየ አቅጣጫ መረጃ ያገኛል፣ በአስተዳደጉም አንጻራዊ ነጻነት አለው፣ በአመለካከትም ቢሆን ይህ የህብረተሰብ ክፍል ወደ ፊት እየመጣ ነው፡፡ ከዚህም አንጻር በታክቲክም ሆነ በአመለካከት ይህን የህብረተሰብ ክፍል መደገፍ የሚያዋጣና አይቀሬነቱን የሚያሳይ ይመስለኛል፡፡
ዋናው የኢህአዴግ የፖሊሲ መሰረት ማታለል ነው፡፡ ‹‹እኔ ከሌለሁ ኢትዮጵያ ትበታተናለች፡፡›› በሚል የምስራቅ አፍሪካንም ሆነ የሶማሊያን የሽብር ሁኔታ እንደ ማታለያ እየተጠቀመ፤ እነሱ የስጋት ፖለቲካ ውስጥ መግባታቸውን ስለሚያውቅ እሳት የማጥፋት ስራ ነበር የሚሰራው፡ ፡ ይህ ግን መሰረታዊ መፍትሄ የሚያመጣ ሳይሆን ነገሮችን እያዳፈነ፣ ችግሩን እያባባሰ በመሆኑ እንዲሁም የጠቅላይነት ፖለቲካን ለቀጠናውም ሆነ ለኢትዮጵያ እየጠቀመ አለመሆኑ የዓለም አቀፍ የፖለቲካ ኃይሎች ተረድተውታል፡፡ አማራጭ የፖለቲካ ኃይልና መሰረታዊ የሆኑ የዴሞክራሲ መመዘኛዎችን ማምጣት፣ መሰረታዊ የሆኑ የዜጎች ልማትና ዴሞክራሲ ማፋጠን፣ በአቻነት የተመሰረተ ግንኙነትን ካልሆነ በስተቀር በጉልበትና በጠብመንጃ የሚደረገው አገዛዝ እንደማያዋጣ የተረዱበት ጊዜ ነው፡፡ አሜሪካኖች አባቶቻቸው የሞቱበት ነገር (the ideals of ower founding fathers) የሚሉት የሰውን ልጅ መብትና የሰብአዊ መብት ማክበር ለሁሉም አገራት መድሃኒት መሆኑን ራሳቸው አፍጋኒስታንና ኢራቅ ውስጥ በነበሩበት ወቅት አይተውታል፡፡ በየመን፣ በምስራቅ አፍሪካዋ ሶማሊያም ቢሆን ተመሳሳይ የእሳት ማጥፋት ፖለቲካ ለውጥ እንዳላመጣ ተገንዝበውታል፡፡ በየ ደረጃው በህዝብ ተሳትፎ የሚያድግ ዴሞክራሲና በዜጎችም ይሁን በአገራት መካከል በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ግንኙነት መምጣት ካልቻለ አፋኝነት እንዳልጠቀመ የተረዱበት ጊዜም ይመስለኛል፡፡