Monday, May 27, 2013

ጥንቃቄ! እባካችሁ ባንተባበር እንኳ አንጠላለፍ!

ጥንቃቄ! እባካችሁ ባንተባበር እንኳ አንጠላለፍ!


አርያ ጌታቸው
ሰማየዊ ፓርቲ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከፍተኛ የሆነ ትኩረትን ሽፋንን በተለያዩ ሚዲያዎች አግኝቱዋል ፡፡ እነዚህን ሽፋኖች ያገኘበትን ምክንያትን ግን አንዳንድ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች “ድርጅቱ የአፍሪካ ህብረትን ስብሰባ ተጥቅሞ በጠራው ሰልፍና እንደማይፈቀድላቸው እያወቁ ለሚዲያ ፍጆታ በማዋላቸው ነው” የሚል እንድምታ በመያዝ የሰልፉን ቀን መራዘምና መተላለፍ እንደ ፖለቲካ ክስረት ቆጥረውታል፡፡ ይህንን ለማስረዳት ፓርቲው ባለፉት አራት ወራት ያደረጋቸውን ጉልህ እንቅስቃሴዎች እና የሚዲያውን ትኩረት ያገኘባቸው ኩነቶች በወፍ በረር ለማየት እንሞክር፡፡Addis Ababa, Ethiopia a call for demonstration
1. የካቲት 3 ቀን 2005 ዓም. በብሔራዊ ትያትር ቤት “መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ” በሚለው የ ፕ/ር መስፍን መጽሃፍ ዙሪያ ሀገሪቷ ውስጥ ያሉ እውቅ ምሁራንን ጋብዞ ያወያየው (አዳራሹ ሞልቶ ሰዎች መመለሳቸውን እንዳትዘነጉ) ከረጅም ጊዜ በሁዋላ እንዲህ አይነት ትልቅ ህዝባዊ ውይይት ሲደረግ የመጀመሪያው ነው፡፡
2. መጋቢት ስምንት ቀን 2005 ዓ.ም ከጠዋቱ 3 ሰዓት ለኢትዮጵያ ተቆርቋሪ የግል ተነሳሽነት ማህበር፤ ሰማያዊ ፓርቲ እና ባለራዕ ወጣቶች ማህበር በጋራ በመሆን “ለፋሽስቱ የጦር ወንጀለኛ ለማርሻል ግራዚያኒ ክብር መስጠት የአባቶቻችን መስዋዕትነት ማራከስ ነው” በሚል የተጠራውን ሰልፍ፡፡ በጊዜው አባላቱና ደጋፊዎቹ ሰልፉ ከመጀመሩ በፊት አመራሮቹ ቀድመው ቦታው ላይ በመገኘት የሰልፉን ሂደት ለማሰማመር ደፋ ቀና ሲሉ 6 የሰማያዊ ስራ አስፈጻሚ አባላት(ሊቀመንበሩን ጨምሮ) እና ታዋቂ ግለሰቦችን የፓርቲው አባላትን ጨምሮ 34 ሰዎችን ፖሊስ በቁጥጥር ስር አውሏቸው ከ 24 ሰዓት በኋላም ፈቷቸዋል፡፡ ይህ ሰላማዊ ሰልፍም አንድነት ፓርቲ ወ/ሪት ብርቱካን ታስራ በነበረበት ወቅት ከተደረገው ሰልፍ በኋላ የመጀመሪያው ነው፡፡ (ከተሳሳትኩ እታረማለሁ)
3. ፓርቲው በዋቢ ሸበሌ ሊያደርገው የነበረው የገቢ ማሰባሰቢያ እና የኢህአዴግን ውንብድናን ያጋለጠበት ቪዲዮና የሶሻል ሚዲያዎች ሽፋን፡፡
4. በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው የተመለሱ ዜጎችን ሁኔታ ለመመልከት የተጓዙት የሰማያዊ ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ይዘውት የተመለሱት ማስረጃ እና በወቅቱ የፓርቲው አመራሮች ለሰኣታት በክልሉ የታጠቁ ኋይሎች መታሰራቸው፡፡
እንዲሁም ፓርቲው በየጊዜው በጽ/ቤቱ የሚያደርጋቸው ውይይቶችና እንቅስቃሴዎች ማለትም ከየካቲት – ግንቦት ባሉት አራት ወራቶች በብዙ ሰዎች እና ሚዲያዎች አይን እንዲገባ አድርጎታል፡፡በነዚህ ሂደቶች ውስጥ አነጋጋሪ ከነበሩት አንኳር ሀሳቦች ውስጥ፤ በአብዛኛው በወጣቶችና በሴቶች ዙርያ መመስረቱ፣ የበርካታ አንጋፋ ምሁራን ይሁንታ ድጋፍ ከጀርባ መኖሩ በተለይ (እንደ ፕ/ር መስፍን፣ ፕ/ር በፍቀዱ፣ ዶ/ር ያዕቆብ፣ ዶ/ር ዳኛቸው፣ ፕ/ር ገብሩ እና አርቲስት ደበበ …)፣ የአመራሮቹ ቁርጠኝነትና በሚኖሩት ማናቸውም ፕሮግራሞች ላይ ግምባር ላይ መገኘታቸውና ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ወደኋላ አለማለታቸው… የመሳሰሉት አንኳር ነጥቦች ጋር የሰሞኑ በግንቦት 17 ቀን የጠሩት ታላቅ ሰልፍ የድርጅቱን ጅማሮ (ጅማሮ ያልኩት ፓርቲው ከተመሰረተ 1አመት ከ6 ወር ብቻ እንደሆነው ለማመልከት ነው) በማየት በሀገር ውስጥ ያለውን የሰላማዊ ትግል እንቅስቃሴ ለወደፊቱም ተስፋ በማድረግ ጭምር ነው፡፡
ፓርቲው በግንቦት 17 ለጠራው ሰልፍ ያስቀመጠው ምክንያት ፓርቲው ከዚህ በፊት አስቸኳይ መፍትሄ እንዲፈለግላቸው ጥሪ ለመንግስት አቅርቦ መልስ የተነፈጋቸውን ጥያቄዎች
1. ጋዜጠኞችን፣ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችንና አባላትን በአሸባሪነት ስም ማሰርና ማሰቃየትን እንዲቆም
2. የዜጎችን ሰብዓዊና ሕገ መንግስታዊ መብቶችን በመጣስ ለዘመናት ከኖሩበት ቦታ ኢሰብዓዊ በሆነ ድርጊት በታጠቁ ኃይሎች እንዲፈናቀሉ ማድረግ የዘር ማጥፋት ወንጀል በመሆኑ የድርጊቱ ፈፃሚዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ
3. የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮችን በአሸባሪነት ወንጀል በመክሰስ በእስር እንዲማቅቁና ሰብዓዊ መብታቸው እንዲጣስ መደረጉ
4. መንግስት የኑሮ ዉድነትን፣ የሥራ አጥነትንና በሙስና የተዘፈቁ የመንግስት ሌቦችን መቆጣጠር አለመቻሉ
ከላይ ያሉትን ምላሽ የተነፈጓቸው ጥያቄዎቻችን የዓለም ዓቀፍ ማሕበረሰብን ትኩረት የሚያገኙበትን መንገድ መፈለግ የሚል ነበር፡፡ ይህንንም ሰልፍ ለማድረግ ከመንግስት ምንም እንኳ ፈቃድ ባያስፈልገውም ማሳወቅ ይጠበቅበት ነበር፡፡ ህጉም በሚያዘው መሰረት ከ48 ሰዓት በፊት ቢያስገቡም የመስተዳድሩ ሃላፊዎች ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመሆናቸው በእማኞች ፊት ደብዳቤውን ጠረጴዛ ላይ ትተውት የሰልፉን ዝግጅት ቀጠሉ፡፡ እዚህ ላይ “ማሳወቅ” የሚለው ጉደይ የገባው ዜጎች ተቃውሟቸውን በሚገልጹበት ወቅት ከተቃራኒ ወገን ጥቃት እንዳይደርስባቸው እና ሰልፉ ወዳልታሰበ ረብሻ እንዳያመራ ጥበቃ ወይም ከለላ ለማግኘት እንዲሁም የትራፊክ ስርዓቱን ለማስተካከከል ለመሳሰሉት ጥንቃቄዎች ሲባል ብቻ እንጂ ሰልፍ ማድረግ በራሱ ፈቃድ አያስፈልገውም፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ መስተዳድሩ ያቀረበው ምክንያት እውነትም ይሁን ውሽት የህግ ክፍተቱን በጠቀም ወይም ህጉን ከለላ በማድረግ ሰልፉን ያራዘመበት መንገድ ሰማያዊ ፓርቲ እንደ አንድ ፖቲካ ተቋም ሊያከብረው የሚገባ ሂደት ከመሆኑም በላይ ፓርቲው መንግስትን ትልቅ ጫና ውስጥ በመክተት ሌሎች ፓርቲዎች የአዳራሽ ውስጥ ስብሰባ ተከለከልን በሚሉበት ወቅት እንዲሁም ፓርቲው ለመስተዳድሩ ያቀረበውን ደብዳቤ ለመቀበል ፈቃደኛ ያልሆኑት አካላቶች፤ የሰላማዊ ሰልፉን ሂደት በመቀበል ደብዳቤ መጻፋቸው (አቤ ቶክቻው እንዳለው ሳይገግሙ) ፓርቲው በመንግስት አካላት ላየ ፈጥሮት የነበረውን ጫና በገሀድ ያሳያል፡፡
ይህ ማለት ግን በራሱ እንደስኬት ሊቆጠር የሚገባው ነው ብዬም አላምንም እንደውም ፓርቲው የበለጠ ትልቅ ውጥረት ውስጥ የሚገባበትና ሀላፊነትን የሚሸከምበት ጊዜ ነው የሚሆነው፡፡ ኢህአዴግ የ 1997 እና 1998 የነበሩትን የሰላማዊ ትግል እና የሰላማዊ ሰልፍ ጥሪዎች እንዴት አድርጎ እንዳጨናገፋቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡ ኢህአዴግ በባህሪው ብዙ ተለዋዋጭ ስልት የሌለው የዛሬ 20 ዓመትም ዛሬም ባለበት የሚሄድ ድርጅት እንደመሆኑ የፊታችን ግንቦት 25 የሚካሄደው ሰልፍ ላይ ምን አይነት እክል ሊፈጥር ይችላል? የሰማያዊ ፓርቲ ዝግጅትስ ምን ይመስላል? የሚለውን በተግባር በሳምት ጊዜ ውስጥ የሚታይ ይሆናል፡፡
ጥንቃቄ! እባካችሁ ባንተባበር እንኳ አንጠላለፍ!!
ፓርቲው ይህንን ሰልፍ ሲጠራ ከጎኑ የፖለቲካ ድርጅቶችና የሺቪክ ማኅበራት አብረውት እንዲቆሙ ጥሪ አቅርቦ የነበረ ቢሆንም በውጭ ከሚገኙ እንደነ አኢጋን በአቶ ኦባንግ የሚመራው፣ የኢትዮጵያ የሽግግር ምክር ቤት ካውንስል፣ በኖርዌይ የሚገኘው አዲስ የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ የመሳሰሉ ተቋማት ካልሆኑ በተለይ ሀገር ቤት ያሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ምንም አይነት ድጋፍ ለማድረግ አለመፈለጋቸው መንገዱ ገና ረጅም መሆኑን ያሳያል፡፡ ሆኖም የየራሳቸው ምክንያት አላቸው ብንል እንኳ ከሰልፉ መራዘም በኋላ ዝምታቸውን በመስበር አንዳንድ ግለሰቦች ነገሩ “የከሸፈ” መሆኑን ለማብሰር ሲሯሯጡ ትንሽ እንኳ ትዝብት ውስጥ እንወድቃለን አለማለታቸው ያሳዝናል፡፡
እባካችሁ ባንተባበር እንኳ አንጠላለፍ !! ይህ ሰልፍ ቁጥሩ ይብዛም ይነስም ከተሳካ አይነጥላችንን የምንገፍበት ነውና ጥቅሙ ለሰማያዊ ብቻ ሳይሆን በሰላማዊ ትግል እንምናለን ለሚሉ ሀገር ውስጥ ላሉ ፓርቲዎች በሙሉ ስለሆነ ከተቻለ ባለው ጊዜ መተባበር ካልተቻለ እጅን መሰብሰብ እላለሁ!!

No comments:

Post a Comment