Monday, February 16, 2015

የዲሞክራሲዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ አጠቃላይ የአባላት ስብሰባ እና የአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ 60ኛ አመት የልደት በአል በተሳካ ሁኔታ ተከናወነ


ፌብርዋሪ 14, 2015 በኖርዌይ የሚኖሩ የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ መተዳደሪያ ደንቡ በሚያዘው መሰረት የአባላት ጠቅላላ 3ኛ እና 4ኛ ሩብ ዓመት መደበኛ ስብሰባ የሥራ ክንውን ሪፖርት የቀረበበት የተሳካ አጠቃላይ ስብሰባ አድርገዋል። በስብሰባው ላይ በኖርዌይ ዋና ከተማ ኦስሎና በተለያዩ የኖርዌይ ከተሞች የሚኖሩ የድርጅቱ አባላቶች የተገኙ ሲሆን የአባላት ስብሰባው አስቀድሞ በተያዘለት ፕሮግራም መሰረት በኖርዌጂያን የሠዓት አቆጣጠር ከቀኑ 13፡30 ተጀምሮዋል።
ስብሰባውን የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት በኖርዌይ ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት አቶ አቢ አማረ በ 24 ዓመት የወያኔ አረመኒያዊ አገዛዝ በግፍ ለተገደሉት እና በየእስር ቤቱ በግፍ ለሚስቃዮ ንጹሀን ዜጐች የአንድ ደቂቃ የህሊና ጹሎት በማድረግ ስብሰባውን ያስጀመሩት ሲሆን በመቀጠልም የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት በኖርዌይ ሊቀመበር አቶ ዮሐንስ አለሙ አባላቱን እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት ንግግር አቅርበው የዛሬው የአባላት ስብሰባ ከሌሎቹ ጊዜያት በሁለት ምክንያቶች የተለየ መሆኑን ለተሰብሳቢው ገልፀዋል ይሄውም፦
1 የአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ 60 ኛ ዓመት የልደት በአል የሚከበርበት ቀን በመሆኑና
2 የዲሞክራሲ ለውጥ በኢትዩጵያ ድጋፍ ድርጅት በኖርዌይ የተመሰረተበትን 10ኛ አመቱ ላይ መገኘቱ እንደሆነ በማስረዳት ድርጅቱ በእነኚህ አስር ዓመታት ውስጥ ብዙ አመርቂ ስራዎችን እንደሰራና ቅንጅት ይዞለት የተነሳው አላማ እስከ አሁን ድረስ ይዞ በመጓዝ ላይ ያለ ድርጅት በመሆኑ ስለዚህም በድርጅታቸው ኩራት የሚሰማቸው መሆኑን በመግለፅ ይህንንም አላማ ከግብ ለማድረስ በድርጅቱ ውስጥ ያሉ ወጣቶች እና ሴቶች እየሰሩ ያለውን ስራ አድንቀው ወጣቶች ወያኔን ከስልጣን ለማስወገድ ትልቅ አስተዋፅኦ ያላቸው በመሆኑ በድርጅቱ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ትግላቸውን አጠንክረው መቀጠል እንዳለባቸው በማሳሰብ አቶ አንድአርጋቸው ፅጌንና በወያኔ መንግስት በግፍ የታሰሩትን የፖለቲካ እስረኞችን በትግላችን እናስፈታለን በማለት ንግግራቸውን አጠናቀዋል።
unnamed (1)

በመቀጠልም የተለያዩ የስራ ክፍል ኃላፊዎች የስድስት ወር የስራ ክንውን ረፖርት ለአባላቱ ያቀረቡ ሲሆን ከበርገን፣ ከስታቫንገር፣ እና ከትሮንዳይም የመጡ የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት በኖርዌይ የስራ ኃላፊዎች በስድስት ወር ውስጥ ስለሰሩት ስራዎች እና ወደፊትም ሊሰሩ ያቀዱትን ስራዎች ለአባላቱ በዝርዝር አስረድተዋል።

Sunday, February 15, 2015

የ2007ቱን ሀገራዊ ምርጫ ሂደት እና ከምርጫዉ ዉጭ ያሉ አዋጭ አማራጮችን በተመለከተ የአርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ የአቋም መግለጫ



pg7-headerአርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሰላማዊ፣ ተዓማኒና ፍትሀዊ በሆነ ምርጫ የማይፈልጋቸውን መሪዎች መሻር፤ የሚፈልጋቸውን ደግሞ መሾም የሚያስችሉትን መሠረቶች ለመጣል የሚታገል ንቅናቄ ነው። እንደሚታወቀው የሕዝብ እውነተኛ ፍላጎት የሚገለጽበት እውነተኛ ምርጫ እንዲኖር ገለልተኛና ቀልጣፋ የፍትህ ሥርዓት፣ የጦርና የፓሊስ ሠራዊት ሊኖሩ ይገባል። ነፃ የሚዲያ ተቋማትና በነፃነት የሚንቀሳቀሱ የሲቪክ ማኅበራት መኖርም መታለፍ የሌለባቸው አቢይ ጉዳዮች ናቸው። አማራጭ ፓሊሲዎችን ማቅረብ የሚችሉ በነፃነት የሚንቀሳቀሱ የፓለቲካ ፓርቲዎች ከሌሉም አማራጮች የሉምና ምርጫ ትርጉም የለውም። ይህ ሁሉ ቢሟላ እንኳን ምርጫውን የሚያስፈጽመው አካል ገለልተኛ፣ ሀቀኛና ተዓማኒ ካልሆነ የሚደረገው ምርጫ የመራጩን ሕዝብ ፍላጎት የሚያንፀባርቅ ሊሆን አይችልም።
ከላይ የተዘረዘሩትን የምርጫ እሴቶች ሙሉ በሙሉ ባይሆንም እንኳን የተወሰኑትን በመጠኑም ቢሆን ያካተተ ምርጫ እንዲኖር መጣርና በሂደት የምርጫውን አፈፃፀም ማሻሻል ይቻል ይሆናል በሚል እምነት የዲሞክራሲ ኃይሎች በህወሓት የሴራ ምርጫዎች ሲሳተፉ ቆይተዋል። ሆኖም በህወሓትና በእውነተኛ ምርጫ መካከል ያለው ተቃርኖ እያደር እየሰፋ ሲሄድ እንጂ ሲጠብ አልታየም። በህወሓት ሙሉ ቁጥጥር ስር በሚካሄድ ምርጫ ኢትዮጵያን የሚጠቅም ለውጥ ሊመጣ ይችላል የሚለው እምነት ለአርበኞች ግንቦት 7 ፈጽሞ የተሟጠጠው ከምርጫ 97 ማግስት ጀምሮ ነው። በግንቦት 7 ቀን 1997 ዓም የኢትዮጵያ ሕዝብ በታላቅ የለውጥ ተስፋ የሰጠው ድምጽ በህወሓት የተዘረፈው ከላይ የተዘረዘሩት ተቋማት ያልነበሩ በመሆናቸው፤ ስለዚህም ከምርጫ በፊት ተቋማቱን መገንባት፤ ተቋማቱን ለመገንባት ደግሞ ህወሓትን ከስልጣን ማስወገድ ይገባል ብሎ በማመኑ ነው አርበኞች ግንቦት 7 በሁለገብ የትግል ስልት በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኘው።
ያም ሆኖ ግን በምርጫ ላይ ያላቸው ተስፋ ፈጽሞ ያልተሟጠጠ ፓርቲዎችን በማክበርና ሥራቸውንም አስቸጋሪ ላለማድረግ ሲባል ከምርጫ 97 ወዲህ የነበሩ ብሄራዊም ሆነ ክልላዊ ምርጫዎችን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከምርጫ ዉጭ ያሉ ሌሎች አማራጮችን ብቻ እንዲመለከት አርበኞች ግንቦት 7 ጥሪ አድርጎ አያውቅም ነበር። አሁን ግን የአገራችን ኢትዮጵያ የፓለቲካ ሁኔታዎች ይህንን የቆየ አቋም በሚያስቀይር መንገድ፤ የአገራችንን የወደፊት ዕድል ብቻ ሳይሆን ባጠቃላይ ያካባቢውን ሰላም በሚጎዳ መልኩ ተቀይሯል። የሰሞኑ የወያኔ እርምጃዎች ትንሽ ተስፋ ያደርግ የነበረውን የዴሞክራሲ ወገንተኛ ተስፋም እምሽክ አድርጎ በልቶታል:: እየተቃረበ ያለው ዓይነት የፌዝ ምርጫ ወያኔ እንደ እንጄራ የራበውን የተቀባይነት እጦት ለአጭር ጊዜ ያስታግስለት ይሆናል እንጂ የሀገሪቱን እያደር እየተወሳሰበ የመጣ ችግር ለጊዜውም እንኳን የሚያስታግስ አይሆንም፤ ይልቁንም ጊዜው በገፋ ቁጥር ችግሩ መቋጠሪያ የጠፋው እየሆነ ይሄዳል::
የሁኔታውን አሳሳቢነት ከግምት ውስጥ በማስገባት የአርበኞች ግንቦት 7: የአንድነትና ለዲሞክራሲ ንቅናቄ አመራር የወቅቱን የአገራችን የፓለቲካ ሁኔታ በጥንቃቄ መርምሮ የሚከተሉት ግንዛቤዎች ላይ ደርሷል።

Wednesday, February 11, 2015

በፕሮፓጋንዳው ስራ በኩል በሚታየው ድከመት ዙሪያ የመንግስት ሹመኞች እርስ በርሳቸው ተካሰሱ


ኢሳትዜና :-በቅርቡ በኪሚኒኬሽን ሚኒስትሩ ሬድዋን ሁሴን በተመራው የቀድመው ኢቲቪ የአሁኑ ኢቢሲ አመራሮች፣ የፕሬስ መምሪያ ሃላፊዎች፣ የኢትዮጵያ ሬዲዮ አመራሮች፣ የህዝብ ግንኙነቶች፣ ኮሚኒኬተሮችና ሌሎች ባለስልጣናት በተገኙበት በተካሄደው ውይይት ላይ የመንግስት የህዝብ ግንኙነት ሰራተኞች የአትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋዜጠኞችን ሲከሱ፣ የኢቢሲ አመራሮች ደግሞ ረጃጅም እጆች ያሉዋቸው ባለስልጣናት ቴሌቪዥኑን ስለተቆጣጠሩት ፍትሃዊ የሆነ ሽፋን ለመስጠት አልተቻለም ሲሉ ወቅሰዋል።
“ረጅም እጅ ያለው ባለስልጣን ካለ፣ ሄክታር መሬትም ቢታረስ ስድስት ጊዜ ዜና ይሰራለታል” በማለት በቅርቡ የተሾሙ የኢቢሲ ባለስልጣን ተናግረዋል
ሌላ ሃላፊ ደግሞ መንግስት በፕሮፓጋንዳው መስክ አጀንዳ ቀርጾ መስጠት አለመቻሉን፣ ከውጭ ተቀርጾ ለሚመጣ አጀንዳ መልስ በመስጠት ላይ ማተኮሩን፣ የህዝብ ግንኙነት ስራው ከአጥቂት ይልቅ ተከላካይ መሆኑንና በማህበራዊ የመገናኛ ብዙሃን አጀንዳ እየቀረጸን ከመከላከል ይልቅ ማጥቃት አለብን ” ብለዋል።
በክልል ጋዜጠኞች መካከል መግባባት እንደሌለ፣ አንዱ ክልል የሌለው ክልል ጉዳይ እንደማይመለከተው፣ የክልል ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የፌደራል ጉዳይም አይመለከተንም ብሎ በክልል የመገናኛ ብዙሃን ዘገባዎች እንደማይቀርቡም ተገልጸሏል
ሚኒስትሮችን ጨምሮ አመራሮች ፌስ ቡክ ቢከፍቱም ፣ የፎቶ አልበም ከመለጠፍ ውጭ የሚሰሩት የለም በማለት አማረው የተናገሩት ሌላ ባለስልጣን፣ ከክልሎች የአማራ ክልል በፌስ ቡክ አጠቃቀም ተሽሎ መገኘቱን ተናግረዋል።
ለኢሳት በደረሰው ሚስጢራዊ የድምጽ ማስረጃ የትግርኛ ክፍል ጋዜጠኞች ደግሞ የአቶ ሃይለማርያምን ቃለምልልስ በመተርጎም፣ እንዲሁም መኢአድና አንድነት ሲለያዩ ዜናውን በደንብ አጉልታችሁ አልዘጋባችሁም ተብለው ሲጨቃጨቁ ይሰማል።
አቶ ሽመልስ ከማልና አቶ ሬድዋን ሁሴን የአሸባሪው ቡድንን የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ መመከት የሚቻለው በጋራ መስራት ሲቻል ብቻ ነው በማለት የተለያዩ ምክሮችን ሰንዝረዋል።
ኢህአዴግ ለፕሮፓጋንዳ ስራ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በእያመቱ እንደሚያወጣ ይታወቃል።
ስብሰባው ላይ ስለተነሱት ጉዳዮች ሙሉ ዝግጅቱን በቅርቡ እናወጣዋለን።