Monday, October 28, 2013

በሰላማዊና በህጋዊ መንገድ ተቃውሞ ቢያቀርቡም የኢህአዴግን ጆሮ ማግኘት ያልቻሉ ተበዳዮች ርምጃ ወሰዱ።

       
በሰላማዊና በህጋዊ መንገድ ተቃውሞ ቢያቀርቡም የኢህአዴግን ጆሮ ማግኘት ያልቻሉ ተበዳዮች ርምጃ ወሰዱ። ሕዝብ ወዶና ፈቅዶ ያልተቀበለው ኢንቨስትመንት ከዘረፋ ተለይቶ እንደማይታይ የአካባቢው ነዋሪዎች አስታውቀዋል። ውድመት የደረሰበት የህንድ ኩባንያ በልማት ባንክ ላይ ኪሳራ ሊያስከትል እንደሚችል ስጋት አለ። ለደረሰው ጉዳት “ተጠያቂው ማን ነው?” የሚል ጥያቄ ተነስቷል። በጥርጣሬ የሚታሰሩ መበራከታቸው በክልሉ ባሉ ተመሳሳይ የእርሻ ኢንቨስትመንት ባለቤቶችን ስጋት ላይ ጥሏል።
ሻይ ቅጠል ለማልማት የተፈጥሮ ጥብቅ ደን እንዲያወድም የተፈቀደለት ቬርዳንታ ሀርቨስት የተባለ ኩባንያ በከፍተኛ ወጪ ያለማውና ለመለቀም በደረሰ ምርት ላይ ማንነታቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች እሳት ለቀውበታል። ጥቅምት 12 ቀን 2006 ዓም ደረሰ በተባለው ቃጠሎ ኩባንያው የደረሰበት ሊሳራ እስከ 80 ሚሊዮን ዶላር ሊደርስ እንደሚችል ስለ ጉዳዩ የሚያውቁ አስታውቀዋል።
አንጋፋ እድሜ ጠገብና ረዣዥም የተፈጥሮ ደን በመጨፍጨፍ ጣውላ እያመረተ ሲቸበችብ የነበረው ኩባንያ ሙሉ ንብረቱና ከፍተኛ መጠን ያለው የጣውላ ምርት ከተለያዩ ማሽኖች ጋር ወድሞበታል። የአካባቢው የጎልጉል ምንጮች እንዳሉት ኩባንያው ላይ የደረሰው የእሳት ቃጠሎ ለመሰብሰብ የደረሰውን የሻይ ቅጠል ማሳ አጋይቶታል።
በጋምቤላ ክልል በመዠንግር ዞን፣ በጎደሬ ወረዳ በጉማሬና በካቦ ቀበሌዎች የሚገኝ 5000 ሄክታር በደን የተሸፈነ መሬት በኢንቨስትመንት ስም እንዲሸጥ መወሰኑን ተከትሎ የአካባቢው ነዋሪዎች ተቃውሞ አሰምተው ነበር። በወቅቱ ውሳኔውን “በባዕድ ወራሪ ሃይል እንኳን የማይፈጸም” በማለት የተቹና ቅሬታቸውን የገለጹ ነበሩ።
ሙሉ በሙሉ በደን የተሸፈነ 3012 ሄክታር ድንግል ለም መሬት በሄክታር111 ብር ሂሳብ ለ50 ዓመት የሊዝ ኮንትራት የተሸጠለት ይህ ኩባንያ ጥብቅ ደኑን ከማውደሙ በፊት ውሳኔው እንዲጤን የአካባቢው ህዝብ በወኪሎቹ አማካይነት ለፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ጥያቄ አቀርበው ነበር። በወቅቱ ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ድርጊቱን በመቃወም የሚከተለውን ጽሁፍ አትሞ ነበር። ሰሚ ባለመገኘቱ የተፈራው ደረሰ።
ጡረተኛው ፕሬዚዳንት ለአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን በሰጡት ትዕዛዝ መሰረት የተፈጥሮ ደኑ ከመጨፍጨፉ በፊት ውሳኔው እንዲመረመርና እንዲጠና ሚያዚያ 28 ቀን 2002 ዓ ም ለክልሉ ደብዳቤ ልኮ ነበር። ሟቹ ጠ/ሚኒስትር በወቅቱ የአፍሪካ የተፈጥሮ ጥበቃና የአየር ንብረት ተሟጋች ነኝ ያሉበት ወቅት መሆኑንን በማስታወስ፣ የፕሬዚዳንቱን መመሪያ በመጠቆም ባለስልጣኑ የጻፈውን የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ የክልሉ ፕሬዚዳንት ህዳር 10 ቀን በተጻፈ ደብዳቤ ደመሰሱት። ከላይ የተጠቀሰው ኩባንያ የ50 ዓመቱን ውል ቅድሚያ ክፍያ የአንድ ዓመት 19 ሺህ ዶላር ስለከፈለ ቦታውን እንዲረከብ ዞኑንን አዘዙ።
የበላይና የበታቹ በማይታወቅበት የመለስ አወቃቀር ጥብቅ ደኑ ያለበት መሬት ለህንዱ ኩባንያ ተላለፈ። ህዝብ ያነሳውን ጥያቄ እስከ ፕሬዚዳንቱ ያደረሱት ሊቀመንበር እንደ ወንጀለኛ ተቆጥረው ከሃላፊነታቸው ተባረሩ። ህዝብ የኑሮው መሰረትና የህይወቱ ያህል የሚንከባከበው ደን ተጨፈጨፈ። የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት ደኑ ሲጨፈጨፍ የነበረው ሃዘን በቃል የሚገለጽ አልነበረም።
ባገኘው ከፍተኛ የደን ምርት ጣውላ ማምረት የጀመረው ኩባንያ መጋዘን ገንብቶ የጣውላ ንግድ ውስጥ ገባ። አሁን ድረስ ንዴቱና የበደል ስሜቱ ያለቀቀቃቸው የአካባቢው ነዋሪዎች የተካሄደባቸውን ግፍ “ዝርፊያ” እያሉ ነው የሚጠሩት።
ህግን ጠብቀው ኢህአዴግን ያሳሰቡት የአካባቢው ነዋሪዎች አሁንም ቢሆን በእስርና በድብደባ በማሰቃየት ኢንቨስትመንትን /ነዋሪዎቹ ዝርፊያ ነው የሚሉት/ በክልሉ ቀጣይ ማድረግ አይቻልም። አስቀድሞ ባቀረቡት አቤቱታ መሰረት ኢህአዴግና ኩባንያው ጆሮ ሰጥተዋቸው ቢሆን ኖሮ እንዲህ ያለ አደጋ ሊፈጠር እንደማይችል አስተያየት ሰጡ አሉ።
92 ሚሊዮን ብር በላይ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ እዳ ያለበት የእርሻ ድርጅት፣ ንብረቱ በእሳት ከወደመ በኋላ የተሸከመው እዳ አጀንዳ ሆኗል። የደረሰበት ውድመት ከፍተኛ በመሆኑ ክልሉንና ኢህአዴግን ካሳ እንደሚጠይቅም ከወዲሁ ተሰምቷል። ዜናውን ያቀበሉ ክፍሎች “ህዝብ ላልተቀበለው ኢንቨስትመንት ካሳና የልማት ባንክ ላይ ለደረሰው ኪሳራ ተጠያቂው ኢህአዴግ ነው” የሚል ጥያቄ መነሳቱን አመልክተዋል።
ለአበባ እርሻ ላስቲክና ኬሚካል በማስያዝ ልማት ባንክን እያለቡ የተሰወሩ በርካታ ድርጅቶችና ለስርዓቱ ቅርበት ያላቸው ሸሪኮቻቸው መኖራቸውን በማስታወስ በጋምቤላ ተመሳሳይ ድርጊት ሊፈጸም እንደሚችል የዜናው ምንጮች ጠቁመዋል። ካራቱሪ በኪሳራ መንገዳገዱን፣ ሼኽ መሐመድ ሁሴን አላሙዲ በ”ውክልና” ለሳዑዲ አረቢያ ቀለብ እንዲያመርት የተከሉት ሳዑዲ ስታርና ሌሎች የህወሃት ሰዎች ከተለያዩ የአገር ውስጥ ባንኮች ከፍተኛ ገንዘብ መበደራቸውን ገልጸዋል።
“ህዝብን ያለፈቃዱ በማፈናቀልና መሬቱን በመቀማት የሚከናወን ኢንቨስትመንት ሁሌም አደጋ ላይ መሆኑ አያጠራጥርም” በማለት የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ አኢጋን ዋና ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ ለጎልጉል ገልጸዋል። “ኢንቨስትመንት እንኳን ደህና መጣህ በሚል ህዝብ ካልተቀበለው ዘረፋ ነው” ያሉት አቶ ኦባንግ “በሰላማዊና በሰለጠነ መንገድ ድምጹን ሲያሰማ ጆሮ ያጣ ህዝብ ተቃውሞውን ገለጸ” በማለት በደረሰው ውድመት ባይደሰቱም ለውድመቱ ተጠያቂው ኢህአዴግና ከኢህአዴግ ጋር ተሻርኮ ዝርፊያ ያከናወነው ድርጅት እንደሆነ አመልክተዋል።
ካሩቱሪና ሳዑዲ ስታርን ጨምሮ ህዝብ ላይ በተፈጸመ ግፍ ሃብት ለማፍራትና ለመበልጸግ የሚያስቡ ትልቅ ግንዛቤ ሊወስዱ እንደሚገባ ያሳሰቡት አቶ ኦባንግ “ኢህአዴግ ዝርፊያና ኢንቨስትመንትን ለይቶ መሔድ ካልቻለ ስጋቱ እየጨመረ ይሄዳልና ከስህተት በመመለስ ህዝብ በሚፈቅደው መልኩ ማስተናገድ ግድ ነው” ሲሉ አሁንም ጆሮ የለውም ለሚባለው ኢህአዴግ ማሳሰቢያ አዘል ምክር ለግሰዋል። ባለሃብት የሚባሉትም ከዚህ ታላቅና አሳዛኝ ውድመት ሊማሩና ህዝብ “እንኳን ደህና መጣችሁ እንዲላቸው ህዝብ ከሚቃወመው ዝርፊያና አሰራር ራሳቸውን ሊያገሉ ይገባል” ብለዋል።

የክልሉ ፕሬዚዳንት ቃጠሎውን ማመናቸውን ሪፖርተር በእሁድ እትሙ ያስታወቀ ሲሆን አጣሪ ኮሚቴ ተቃቁሞ አደጋውን ያደረሱት እነማን ናቸው የሚለው እየተመረመረ እንደሆነ ጠቁሟል። የክልሉ የጎልጉል ምንጮች በርካታ ሰዎች እሳት አስነስታችኋል በሚል መታሰራቸውና በፌዴራል አንጋቾች እየተመረመሩ መሆኑን አረጋግጠዋል። እሳት ያስነሱትን ለማጋለጥ በሚል በየመንደሩ በሚደረግ ማዋከብ ነዋሪዎቹ መማረራቸውን ተናግረዋል። ለጊዜው የእስረኞች ቁጥር ባይታወቅም ወደ ማዕከል የተላኩ በርካታ እንደሆኑም ገልጸዋል። በማያያዝም ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ ኢህአዴግም ሆነ ማንም ተጠቃሚ ስለማይሆን ህዝብን ማዳመጥ ሊቀድም እንደሚገባው ጠቁመዋል። (ፎቶ፡ ለማሳያነት ብቻ)

Sunday, October 27, 2013

“ኢቴቪ” የዜና መረጃዎችንና የሰዎችን መልክ ይደፈጥጣል

በኢቴቪ የምናያቸው ቪዲዮዎችና ምስሎች፣ የተደፈጠጡና የተጣመሙ ሆነዋል – ስንት ወሩ? አልተስተካከለም።
በኢቴቪ የሚሰራጩ የተዛቡና የተሳሳቱ ዜናዎች ወይም ዘገባዎች ያሳፍራሉ፤ ደግሞም መላ ያለው አይመስልም።
አንዳንዴ፣ በኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቪዥን የሚሰራጩ ዜናዎችን መስማት ያሳቅቃል፤ ወይም ያዝናናል። በሌላ በኩል ደግሞ ቀሽም ስህተት ስለሆነ ያዝናናል። ከግማሽ ምዕተ አመት በላይ እድሜ ያስቆጠሩ የአገሪቱ ብቸኛ የቴሌቪዥንና የሬድዮ አንጋፋ ድርጅቶች መረጃ ሲሳሳቱና ሲያዛቡ ማየት ያሳቅቃል። 
ባለፈው ረቡዕ ምሽት የተሰራጨውን ዜና መጥቀስ እችላለሁ። በአፍጋኒስታን የተሰማራው ሰላም አስከባሪ ሃይል አገሪቱን ለቅቆ የሚወጣበትን የጊዜ ገደብ ለመቁረጥ እንዳልቻለ የሚገልፅ ነው ዜናው። ሰላም አስከባሪው ሃይል ወደ አፍጋኒስታን የተሰማራው፣ በእርስበርስ ግጭት መነሻነት እንደሆነም ዜናው ይጠቅሳል። የአሜሪካ እና የአጋሮቿ ጦር ሃይል ወደ አፍጋኒስታን ለምን እንደተሰማራ ተረሳ ማለት ነው? አስር አመት ያስቆጠረ ዘመቻ ስለሆነ ኢቲቪ አያስታውሰው ይሆናል፡፡ ግን፤ እንዴት እንዴት የቢን ላደንና የአልቃይዳ ሽብር ሊረሳ ይችላል? በኒውዮርክና በዋሺንግተን የ3ሺ ሰዎችን ህይወት የቀጠፈ የሽብር ጥቃት መፈፀማቸውስ እንዴት ይዘነጋል? ከዚያ በኋላ፣ በአሜሪካ መሪነት፣ በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ወታደሮች ወደ አፍጋኒስታን መዝመታቸውን መላው አለም ያውቀዋል፡፡
ለኢቲቪ እንዴት እንደተሰወረበት እንጃ! አናስታውስም? ለአመታት በመንዛዛቱ “ዘመቻነቱ”ና ውጤታማነቱ ቢደበዝዝም፣ በጊዜው ትክክለኛ እርምጃ ነበር። 
የሆነ ሆኖ፣ የአሜሪካ ዘመቻ ቢን ላደንን ለመግደል፣ አልቃይዳን ለመውጋትና ጥላ ከለላ የሆናቸውን የታሊባንን ሃይል ከስልጣን ለማስወገድ እንጂ፣ “ሰላም ለማስከበር” የተካሄደ ዘመቻ አይደለም። በአጭሩ፣ ለጦርነት ነው፣ አሜሪካና አጋሮቿ ወታደሮቻቸውን ያዘመቱት። በእርግጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ የወታደሮቹ ቁጥር ቀንሷል። ነገር ግን፣ ዛሬ ከአስር አመት በኋላም፣ ገሚሶቹ ከአሜሪካ፣ ቀሪዎቹ ደግሞ ከሌሎች የኔቶ አባል አገራት የተውጣጡ ወደ መቶ ሺ የሚጠጉ ወታደሮች በአፍጋኒስታን እንደተሰማሩ ናቸው። ሰላም አስከባሪ የሚሰማራው ደግሞ፣ “ሰላም ሰፍኗል” ተብሎ ሲታሰብ ነው – “ሰላምን ለመጠበቅ”። የተባበሩት መንግስታት ሰላም አስከባሪ ሃይል ወደ ሶማሊያ ያልተሰማራው ለምን ሆነና? በአገሪቱ ሰላም የለም፣ ሰላም ከሌላ ሰላምን ማስከበር አይቻልም በሚል ነው። ታዲያ የአፍሪካ ህብረት፣ ለምን “ሰላም አስከባሪ ሃይል” አሰማራ? “የተወሰነ ሰላም ተገኝቷል” ብሎ ስላመነ ነዋ። 
በአፍጋኒስታን ግን፣ የሰላም አስከባሪ ሃይል የማሰማራት ሃሳብ በጭራሽ ተነስቶ አያውቅም። ሰሞኑን ስለ አፍጋኒስታን እና ስለ አሜሪካ ወታደሮች የሚያወሱ በሺ የሚቆጠሩ ዜናዎችና ዘገባዎች ቢሰራጩም፣ በአንዳቸውም ላይ “ሰላም አስከባሪ ሃይል” የሚል አባባል አታገኙም – በኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቪዥን ድርጅት በተሰራጨው ቀሽም ዜና ካልሆነ በቀር። በእርግጥ፣ ዜናውን የሰራው ጋዜጠኛ ቀሽም ላይሆን ይችላል። ደግሞም፣ በዜናው የተካተቱ በርካታ መረጃዎች ሲታዩ፣ ጋዜጠኛው ቀሽም እንዳልሆነ ይጠቁማሉ። ቀሽም ስህተት እንዳይፈጠር የሚከላከል አሰራርና ባህል በድርጅቱ ውስጥ አለመኖሩ ይመስለኛል – ዋናው ችግር።
“የሜርከል ፓርቲ አሸነፈ፣ ፓርቲያቸው ተሸነፈ”
በቅርቡ በጀርመን በተካሄደው ምርጫ በአብላጫ ድምፅ ያሸነፈውና በአንጌላ ሜርከል የሚመራው ፓርቲ፤ አዲስ መንግስት ለመመስረት ውይይት እያካሄደ ነው። ሲዲዩ የተሰኘው ፓርቲ ከነአጋሩ፣ በምርጫው 42 በመቶ ድምፅ አግኝቷል። ታዲያ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ሬዲዮ የተሰራጨው ዜና ምን ይላል አትሉም? ቀደም ብሎ እንደተጠበቀው የአንጌላ ሜርከል ፓርቲ በምርጫው ሲያሸነፍ፣ ተፎካካሪው ሲዲዩ ፓርቲ 42 በመቶ ድምፅ በማግኘት ተሸንፏል ይላል ዜናው። ትክክል ይመስላል። ከሃምሳ በመቶ በታች ድምፅ ያገኘ ፓርቲ በተሸናፊነት መጠቀሱ አይገርምም። ቀሽሙ ስህተት ምን መሰላችሁ? ሲዲዩ የአንጌላ ሜርከል ተፎካካሪ ፓርቲ አይደለም፤ አንጌላ ሜርከል የሚመሩት ፓርቲ ነው። አሸነፈ እንጂ አልተሸነፈም፡፡ በኢቴቪ አዘጋገብ…”አቶ ኃይለማርያም የሚመሩት ፓርቲ በምርጫው ሲያሸንፍ ኢህአዴግ ተሸንፏል” እንደማለት እኮ ነው፡፡
የአንጌላ ሜርከል ፓርቲ (ሲዲዩ) ከነአጋሩ 42 በመቶ ድምፅ በማግኘቱ ነው፣ በአብላጫ ድምፅ አሸናፊ ለመሆን የቻለው። ዋናው ተፎካካሪ ፓርቲ (ኤስፒዲ) ደግሞ 25 በመቶ ገደማ ድምፅ አግኝቷል። 9 በመቶ፣ 8 በመቶ፣ እና ወደዚያው ገደማ ድምፅ ያገኙ ሌሎች ፓርቲዎችም አሉ። የአንጌላ ሜርከል ፓርቲ በአሸናፊነት የሚጠቀሰው፣ መንግስት ለመመስረት ከአንድ ፓርቲ ጋር ጥምረት መፍጠር ስለሚበቃው ነው። ተቀናቃኛቸው ኤስፒዲ ፓርቲ ግን፣ ከአራት ወይም ከአምስት ፓርቲዎች ጋር ጥምረት ካልፈጠረ፣ መንግስት ለመመስረት የሚያስችል አቅም አይኖረውም። እንግዲህ፣ የአንጌላ ሜርከል ፓርቲ በአብላጫ ድምፅ ሲያሸንፍ፣ ተፎካካሪው ሲዲዩ ፓርቲ 42 በመቶ ድምፅ ተሸንፏል የሚለው ዜና፤ በቀሽም ስህተት ሳቢያ ምን ያህል መረጃውን ሁሉ እንዳዛባው አያችሁ?
የአካባቢው ጥበቃ ሟርትና የዩኤን እዬዬ 
በዚሁ ወር የተሰራጨ ሌላ ዜናም ልጥቀስላችሁ። “ከአካባቢ ጥበቃ” ጋር. በተያያዘና የአለም የሙቀት መጠንን በተመለከተ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስር፣ በየጊዜው ጠቅላላ “ሳይንሳዊ” ሪፖርት አዘጋጅቶ የሚያቀርብ ድርጅት አለ። በእርግጥ፣ የአካባቢ ጥበቃ ጉዳይ፣ በአመዛኙ “ከፖለቲካ እምነት” ጋር እንጂ፣ “ከሳይንሳዊ እውነታ” ጋር ብዙም አይዛመድም። ምን ለማለት እንደፈለግኩ ልንገራችሁ፡፡ “ሟርት” ማስተጋባት የማይሰለቻቸው የአካባቢ ጥበቃ ቡድኖች፤ ከሰላሳ አመት በፊት፣ “አለም በቅዝቃዜ ደንዝዛ በበረዶ ትሸፈናለች” በማለት ነበር ዘመቻ የሚያካሂዱት። ነገር ግን፣ የተነበዩለት “Global Cooling” በእውን አልተከሰተም። ግን ሌላ ትንበያ አላጡም። አለምን የሚያሰጋት፣ የበረዶ ቅዝቃዜ ሳይሆን፣ የዓለም ግለት “Global Warming” ነው ተባለ።
በእርግጥም፣ የአለም አማካይ ሙቀት፣ በመቶ አመታት ውስጥ በግማሽ ሴንቲግሬድ እንደጨመረ የተለያዩ የሳይንስ ምርምሮች ይመሰክራሉ። የአካባቢ ጥበቃ ቡድኖች ግን፣ ሳይንሳዊ ግኝት ላይ ሳይሆን፣ ከሟርት ያልተለየ ትንበያ ላይ ነው የሚያተኩሩት። በመቶ አመታት ውስጥ የአለም ሙቀት እስከ 5 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ይጨምራል በማለት አለምን የሚያስበረግግ “እዬዬ” ማስተጋባት፣ የቡድኖቹ የእለት ተእለት ስራ ነው። “እዬዬ”ውን በአስለቃሽነት እያስተባበረ የሚመራው ደግሞ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ነው – በየጊዜው በሚያዘጋጃቸው ጠቅላላ “ሳይንሳዊ” ሪፖርቶች። 
የ“ሟርት” ነገር! ዩኤን እና የአካባቢ ጥበቃ ቡድኖች የተነበዩት ያህል የአለም ሙቀት አልጨመረም። በተለይ ባለፉት 20 አመታት፣ ከቁጥር የሚገባ ጭማሪ አላሳየም። ለዚህም ይመስላል፣ “የአለም ግለት” ከሚለው ስያሜ ይልቅ፣ በደፈናው “የአየር ንብረት ለውጥ” “Climate Change” የሚል ፈሊጥ ያመጡት። አምስተኛው ጠቅላላ “ሳይንሳዊ” ሪፖርት በቅርቡ የተሰራጨውም፣ በዚህ ድፍን ስያሜ ነው። ከቀድሞዎቹ ሪፖርቶች ብዙም የተለየ አይደለም፤ ትንሽ ለየት የሚለው፣ ባለፉት 20 አመታት የአለም ሙቀት እንደተጠበቀው አለመጨመሩን ለመካድ አለመድፈሩ ብቻ ነው። ከተጠበቀውና ከተተነበየው ጋር ሲነፃፀር፣ ከሶስት እጥፍ በታች ነው የሙቀት ለውጥ የተመዘገበው። ከሪፖርቱ ጋር በተያያዘ የተሰራጩ ዓለማቀፍ ዘገባዎችም፣ ይህንን አወዛጋቢ መረጃ በስፋት ጠቅሰውታል። የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት (ኢሬቴድ) ግን፣ ጨርሶ ጉዳዩን አላነሳም። እናስ ምን ዘገበ? በተባበሩት መንግስታት አስተባባሪነት የሚሰራጨው ሪፖርት ውስጥ የተካተቱ የዓለም ግለትን የሚመለከቱና ዓለምን የሚያስበረግጉ ወሬዎችን ነዋ። ግን ምን ዋጋ አለው? የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት እነዚህን ጎደሎ መረጃዎችንም ቢሆን በትክክል አልዘገባቸውም። እንዴት በሉ።
እንደሚታወቀው፣ በዩኤን እና በአካባቢ ጥበቃ ቡድኖች ድምዳሜ መሰረት፣ የአለም ግለት መንስኤ የሰዎች አኗኗር ነው። በተለይም በነዳጅ አጠቃቀም የሚፈጠረው ካርቦንዳይኦክሳይድ፣ ለአለም ግለት ዋነኛ መንስኤ ነው ይላሉ።
ምን ያህል እርግጠኞች ናችሁ ተብለው ሲጠየቁ፣ በአብዛኛው እርግጠኛ ሆነናል የሚል ምላሽ ነበር የሚሰጡት። ከቅርብ አመታት ወዲህ ደግሞ፣ “በጣም እርግጠኞች ነን፤ 90 በመቶ እርግጠኞች ነን” ወደ ማለት ደረሱ። በዘንድሮው ሪፖርት ደግሞ፣ “እጅግ በጣም እርግጠኞች ነን” ወደ የሚል ደረጃ ተሸጋግረዋል። የአለም ግለት በሰዎች አኗኗር ሰበብ እንደተከሰተ 95 በመቶ እርግጠኞች ሆነናል ይላል ሪፖርቱ። የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ግን፤ የአለም ግለት 95 በመቶ ያህሉ በሰዎች አኗኗር ሰበብ የሚከሰት ነው ብሎ ዘገበው። ምን እንደማለት መሰላችሁ? “የእገሌ ቡድን የተሸነፈው በተጨዋቾች አሰላለፍ ሳቢያ እንደሆነ እርግጠኛ ነኝ፤ 95 በመቶ እርግጠኛ ነኝ” ሲባልና፣ “የእገሌ ቡድን ለሽንፈት የተዳረገበት ምክንያት 95 በመቶ ያህሉ ከተጫዋቾች አሰላለፍ የመነጨ ነው” ሲባል ልዩነት የለውም?
ምናልባት ይህንን ልዩነት ማወቅ ይከብድ ይሆናል። አንዳንዴ ግን፣ የኢቴቪ ቀሽም ስህተቶች የሚመነጩት ካለማወቅ ብቻ አይደለም። ይህችን ቅንጣት ስህተት ተመልከቱ። ጠ/ሚ ኃይለማሪያም ደሳለኝ፣ በኒውዮርክ ከተለያዩ ባለሃብቶች ጋር ባደረጉት ውይይት ስለኢትዮጵያ ኢኮኖሚና ስለኢንቨስትመንት እድሎች ገለፃ አድርገው አልነበር? በውይይቱ የተሳተፉ አንድ ባለሃብት፣ ለኢቴቪ አስተያየታቸውን ሲሰጡ፣ በገለፃው “intrigued” ሆኛለሁ አሉ – በእንግሊዝኛ። በኢቲቪ ሲተረጎም፣ “በገለፃው ተደስቻለሁ” ተብሎ ቀረበ። የባለሃብቱ አነጋገር ግን፣ “ገለፃው ትኩረቴን ስቧል”፤ “ገለፃው፣ የማወቅ ጉጉት አሳድሮብኛል” ከሚል ሃሳብ ጋር የጥርጣሬ ስሜትንም ጭምር የሚያስተላልፍ ነው። “ገለፃው ጥያቄ አጭሮብኛል” እንደማለት አይነት። ይሄ ነው፤ “በገለፃው ተደስቻለሁ” ተብሎ የተተረጎመው። የአላዋቂነት ስህተት ነው ወይስ ከፕሮፓጋንዳ ፍቅር የሚመነጭ ስህተት? የሆነ ሆኖ ስህተት ነው።
እንግዲህ፣ በጥቂት የዜና ስርጭቶች ውስጥ የታዘብኳቸው ቀሽም ስህተቶችን ነው ያካፈልኳቸው፡፡ ታዲያ እነዚህን ስህተቶች ማስተካከል ለኢቴቪ ይከብደዋል? ላይ ላዩን ስታዩት ከባድ አይመስልም። ነገር ግን፣ ወጣትና ጎበዝ ጋዜጠኞች የሚያጋጥሟቸው ቀሽም ስህተቶችን ማስተካከል የሚቻለው፣ ሙያውንና ሙያተኛውን የሚያበለፅግ አሰራር በማዳበር ነው። ይሄ ደግሞ ከባድ ነው። የረዥም ጊዜ ጥረትንና ፅናትን ይጠይቃል። ታዲያ ይሄ ነገር ኢቴቪ ውስጥ ይኖራል ተብሎ ይታሰባል? አይመስለኝም። የመንግስት ድርጅት ነዋ፡፡ 
ሌላውን ተዉት። ኢቴቪ የዜና እና የዘፈን ክሊፖችን ሳይቀር፣ ምስሎችንና ቪዲዮዎችን እየደፈጠጠ ማሰራጨት ካዘወተረ ስንት ወሩ ነው? የተለያዩ የቪዲዮ ፎርማቶች፣ በቁመታቸውና በወርዳቸው እንደሚለያዩ ማወቅኮ፣ የቴሌቪዥንና የቪዲዮ ‘ሀሁ’ ነው። በአንዱ ፎርማት የተዘጋጀ ቪዲዮ፣ በሌላ ፎርማት ከተሰራጨ… ወይ የተደፈጠጠ ድንክ ይሆናል ወይም ወደ ላይ የተመዘዘ ሞላላ ሆኖ ይታያል። ያው እንዳያችሁት የስንቱ ሰው መልክና ቁመና፣ በኢቴቪ ሲደፈጠጥ ከርሟል። አሁን፣ ቪዲዮዎችን በትክክለኛ ፎርማት ማሰራጨት ትልቅ ስራ ሆኖ ነው? ግን ለወራት አልተስተካከለም። ይህችን ለማስተካከል የሚበቃ የአፍታ ጥረትና ፅናት ካልተገኘ፤ ሌሎችን ስህተቶች ለማረም የረዥም ጊዜ ጥረትና ፅናት ከወዴት ይመጣል?

ትክክለኛው የኢትዮጵያ ካርታ ኤርትራ በተገነጠለችበት ወቅት መሆን ያለበት ይህ ነበር።

ትክክለኛው የኢትዮጵያ ካርታ፡ በሊግ ኦፍ ኔሽን የሚታወቀውና፡ እንደአውሮፓ አቆጣጠር በ1961 የተባበሩት መንግሥታት ካጸደቃቸው ሦሥቱ የኤርትራ ሁኔታ ውሳኔ፡ ” ኤርትራ የፊዴሬሽኑን ሁኔታ ሕዝቡ ካልፈለገና ካርታዋ ከተገነጠለች፡ ኢትዮጵያ በሊግ ኦፍ ኔሽን ወደሚታወቀው እዚህ ላይ ወደሚታየው ካርታዋ ይመለሳል ነበር። 
የኢትዮጵያውያን ጠላት የነበረው የፋሽስት ወያኔ ሞተር መለስ ዘባንዳዊ፡ ወደብ ሸቀጥ ነው በሚል የብልግናና የውንብድና ንግግሩ፡ ኢትዮጵያውያን የሚከፍሉትን የግብር ገንዘብ ለጂቡቲ በቀን ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚገብር ታውቃላችሁን? 
በውጭ ሃገር የሚገኘው ታላቁ የኢንተርኔት ሚዲያ ” ኢትዮሚዲያ ” በፊተኛው ገጹ ላይ ” ከአርባ ግድብ አንድ ወደብ ” በማለት ለተወናበደው ምስኪኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለማስገንዘብ ነው።በትክክለኛው በነአጼ ምኒልክም ይሁን በሊግ ኦፍ ኔሽን እንዲሁም የኤርትራ ፌዴሬሽን በጸደቀ ወቅት መገንጠልን ሕዝቡ የሚፈልግ ከሆነ፡ በተባበሩት መንግሥታት የሚታወቀው ይኸው ካርታ ነው። ወያኔዎች ስለድንበርም ይሁን ስለባሕር በር የመሃይማን፤ የጫካ አፈራሽ ዱርዬዎች ናቸው።
መለስ ዘባንዳዊ ወደብ ሸቀጥ ነው ብሎ ለጂቡቲ በቀን 6 ሚሊዮን ብር የኢትዮጵያ ሕዝብ የግብር ገንዘብ እንዲጠፋ ያደረገውና ኢትዮጵያን ጭለማ ያደረገው።
ታላቁ የኢትዮጵይውያን የውጭ ኢንተርኔት “፡ኢትዮሚዲያ የፊት ገጽ ላይ የተጻፈው፦ ” ከአርባ ግድብ አንድ ወደብ ” እውነት ነው። በወያኔ ኢትቪና ሌላችም ፕሮፓጋናዳዎች የተወናበደው በተለይም የመከላከያ ሠራዊት ነኝ ለኢትዮጵያ ቆሜያለሁ የሚል ካለ እውነታው ይኸው ነው።

Friday, October 25, 2013

የአንድነት አመራር አፈና እና ድብደባ ተፈጸመባቸው

       

የአንድነት አመራር አፈና እና ድብደባ ተፈጸመባቸው ——————————- የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የብሄራዊ ምክር ቤት አባልና በሚሊዩኖች ድምጽ ለነጻነት ሕዝባዊ ንቅናቄ በተለያዩ ከተሞች በመንቀሳቀስ ከፍተኛ ተሳትፎ ያደረጉት መምህር አበበ አካሉ ትናንት 14/02/06 ዓ.ም የደህንነት መስሪያ ቤት አባላት ነን ባሉ ሶስት ቅጥረኞች የግድያ ሙከራና አካላዊ ጥቃት እንደደረሰባቸው ለፍኖተ ነጻነት ይፋ አድርገዋል፡፡ ሰላማዊው ታጋይ እንደተናገሩት በምሳ ሰዓት ኮተቤ መሳለሚያ አካባቢ ለስራ ጉዳይ ሲንቀሳቀሱ ህገ ወጦቹ ያካራክሯት የነበረችን ላንድክሩዘር መኪና የእግረኛ መንገድ እንድትዘጋ በማድረግ አቶ አበበን በሀይል በመኪናው በመጫን ወደማያውቁት ሰዋራ ቦታ በመውሰድ ቤቶች በሚሰሩበት አካባቢ ከመኪናዋ በማውረድ ሺሚንቶ ላይ በማስተኛት በሰላማዊ መንገድ የሚያካሂዱትን ትግል እንዲያቆሙ ይህ ካልሆነም‹‹ በሽብርተኝነት በመወንጀል መንግስትን በሀይል ለማውረድ ትሰራለህ›› በማለት እንደሚወነጅሏቸው በመንገር በቃላት ለምግለጽ በሚቸግር ሁኔታ ድብደባ እየተፈራረቁ እንዳካሄዱባቸው ተናግረዋል፡፡ መምህር አበበ ከቀኑ 6፡30 እስከ ምሽቱ 1፡00 ሰዓት ግለሰቦቹ ሽጉጥ ደግነውባቸውና የማያውቁትን የአልኮል ቃና ያለው ፈሻሽ ነገር በመጋትና ከሲሚንቶ ጋር አጣብቀው በመርገጥ የግድያ ሙከራ ካደረጉበቫቸው በኋላ ከምሽት ላይ በመኪና አውጥተው እንደጣሏቸው ለፍኖተ ነጻነት ተናግረዋል፡፡ ፍኖተ ነጻነት ፓርቲው አመራሩ በህገ ወጥ መንገድ መያዛቸውንና መደብደቡን በተመለከተ ምን እያደረገ ነው በማለት የፓርቲውን ከፍተኛ አመራሮች በመጠየቅ ከአመራሮቹ ‹‹ጉዳዩን በማጣራት ላይ እንገኛለን፡፡አውሬነት የተሞላበትን አስነዋሪ ድርጊትም በቸልታ የምናልፈው አይሆንም››የሚል ምላሽ አግኝታለች፡፡ መምህር አበበ አካሉ በአሁኑ ወቅት በመኖሪያ ቤታቸው ተኝተው ይገኛሉ፡፡ ሰላማዊው ታጋይ ባለትዳርና የሶስት ልጆች አባት ናቸው፡፡

Thursday, October 24, 2013

አሸባሪነት እና አተረጓጎሙ !!!!!

       




ወያኔ ለእኛ የሾማቸዉ እራሳቸዉን በእኛ ላይ የሾሙ ካድሬዎች የቅጂ መብትን ከመጣሳቸዉ ያፈፃፀም ስህተታቸዉ የስህተትን ድንበር እየተሻገረ ስለሆነ በህግ ልንላቸዉ ይገባል ያለመከሰስ መድታቸዉን ከካድሬዎቹ ላይ ያንሳልንና፤(ልብ ልንለዉ የሚገባዉ ያለመከሰስ መብት በህግ የተሰጣቸዉ ህዝብን ወክለዉ ፓርላማ የገቡ ብቻ ናቸዉ) የዛሬዎቹ ግን ያለመከሰስ መብታቸዉ ለገዢ ከወገኑ እስከ ቀበሌ የወረደ ይመስላል፡፡
ወደ ዋና ጉዳዬ ስመለስ ሰሞኑን በሰዉ በሰዉ የማዉቃቸዉ የጋራ መኖሪያ ቤት የደረሳቸዉ ቤቱን ተረክበዉ የመጨረሻ የማጠናቀቂያ ስራ እየሰሩ ሳለ አንዱን ሲያጠናቅቁ ወደ ሌላዉ ሲገቡ በስሜት እየሆኑ የጋራ መኖሪያዉን ህግ እየዘነጉ ዉበትን እያሰቡ ግንባታዉን ያጣጡፉት ቀጠሉ(ባለቤቶቹ የህንፃ ግንባታ ባለሙያ ናቸዉ) ስራዉን የሚሰሩት አንድም ዉበትን አንድም በህንፃዉ ላይ የነርሱ ቤት ያለዉን ክብደት ለመቀነስ አብዛኛዉን በመስታወት የመጠቀም ስራ ነበር የሰሩት ስራዉም ተጠናቋል፤ … … የሰፈር ደንብ አስከባሪ 10 እና 20 ብር ሲቀበል ፣ ሲያሰራ ከርሞ መጨረሻ ላይ ወይ የተቀበለዉ አላረካዉ ወይ በቅናት ወይ ለህግ ተገዢነቱ ትዉስ ብሎበት በአስቸዃይ አፍርሱት ይላቸዋል፡፡ ይኸ ነገር ከመኖሪያ ሰፈሩ ተነስቶ ቀበሌ፣ ከቀበሌ እንደገና ይነሳና ቤቶች ልማት፣ ክፍለከተማ … እያለ ይቀጥላል፤…. …. የቤት ባለቤቶቹ (ተከሳሾች) እሺ አጥፍተናል! እኛ ስንጀምረዉ ብዙዎቹ የሚመለከታቸዉ ሰወች አይተዉታል አሁን አፍርሱ ብለዉ የሚማገቱን በስፍራዉ ነበሩ የምንሰራዉ ስህተት መስሎ ስላልታየን ግንባታዉን ከምናፈርስ መቀጣት ያለብንን እንቀጣና ቤቱ ባለበት እንቀጥል ብለዉ ሃሳባቸዉን ቢገልጡላቸዉ ሊሰሙአቸዉ አልቻሉም እንዲያዉም እስጣገባ ዉስጥ ገብተዉ ነገሩ ተጠምዞ የፈረደባቸዉ ባለራዕዩ ጠቅላይ ሚኒስተር በማያገባቸዉ ገብተዉ እሳቸዉ የመረጡትን ፕላን እናንተ ማን ስለሆናችሁ ትቀይሩታላችሁ? እንደያዉም አሸባሪዎች ናችሁ እንዲህ አይነት ስራ ከአሸባሪነት ተለይቶ አይታይም ተብለዉ በትርጉም አልባ ቃላታቸዉ ሰዉን መፈረጅ ሲፈልጉ በቃላት በሚዋጉት ካድሬዎች አሸባሪ ተብለዉ ተፈርጀዉ ግንባታዉን እንዲያፈርሱ ታዘዉ ተመለሱ፡፡ እስኪ ነገሮችን በቅንነት እናስበዉ፣ እንከባበር አንድ ሰዉ መሪ ስለሆነ ሁሉን አዋቂ ነዉ ብለንም አንመን ምናልባት የፖለቲካዉ መሃንዲስ እንደሆነ እንጂ በፍፁም የህንፃ መሃንዲስ ይሆናል ማለት ዘበት ነዉ፣ መጥቀስም አስፈላጊ ከሆነ የሞተ ሰዉ ለቀቅ አርገን በነዋሪዎች እንማል ራዕያችንም ግባችንም እስከመቼ ነዉ ሙት የሚሆነዉ? እናንተ ማን ናችሁ ላሉት መሃንዲሶች መሆናቸዉን ዘንግተዉት አይመስለኝም ክፉ መንፈስ ተፀናዉቶአቸዉ ካልሆነ በቀር እንዃን ከጠያቂዎቹ ከተባለዉም ሰዉ በሙያቸዉ ይሻላሉ ብዬ አምናለሁ፡፡
እስኪ በዚህ አገር ህግ ሲወጣ ህዝብ ማዕከል ያደረገ የሚሆነዉ መች ነዉ? ህዝቡስ ይህ ጉዳይህ ስለሆነ እንመካከር የሚባለዉስ? ህዝቡ ይዞት የመጣዉ መቼ ነዉ ተቀባይነት የሚያገኘዉ? መቼ ነዉስ ከመፈረጅ የሚድነዉ?(አሸባሪ፣ ነፍጠኛ፣ አደገኛ ቦዘኔ፣ሙሰኛ፣…) ህጋችንስ ባህላችንን አገናዝቦ ህዝቡን ግምት ዉስጥ ከቶ ካለዉ ነባራዊ ጉዳይ አንፃር ጋር ተዛምዶ በእናዉ ሰዉ ለእናዉ የሚወጣዉ መቼ ነዉ? ከቀጪነቱ(ከተበቃይነቱ) ባለፈ አስተማሪ(አንዱ ካንዱ ሳይጣረዝ) የሚሆነዉ መቼ ነዉ?በጋራ ጉዳያችን በጋራ የምንወስነዉ መቼ ነዉ?ሁሌ መቼ ነዉ እኛ ለአገር የማናስብ፣ አጥፊ፣ አሸባሪ፣ ሌባ ፣ ወንበዴ፣… የሚለዉ አስተሳአብና ትርጓሜ የሚነሳልን?
የሆነዉ ሆነ ግን እስኪ እያንዳንዱን ትርጓሜ እናጢነዉ (ኪራይ ሰብሳቢና ጉቦ እስኪ ምን ያገናኛቸዉ ነበር?) ልብ አርጉ የቀጣዩ ትዉልድ ዕጣ ፈንታ በእጃችን ነዉ፤ ቀጣይ ትዉልድ የምናፈራ እንጂ የምናጠፋ አንሁን!

Wednesday, October 23, 2013

በሁለት የቀድሞ የህወሀት ባለስልጣናት ቤቶች በርካታ የጦር መሳሪያዎች መገኘታቸውን አቃቢ ህግ ገለጸ

 ጥቅምት ፲፫(አስራ ሦስት)ቀን ፳፻፮ / ኢሳት ዜና :-በኢትዮጵያ ህግ አንድ ግለሰብ ከመንግስት በማስፈቀድ አንድ የነፍስ ወከፍ መሳሪያ እንዲይዝ ቢፈቀደልትም ፣ በተግባር ግን አብዛኛው ህዝብ በመሳሪያ አሰሳ ስም የግል መሳሪያውን መቀማቱን በተለያዩ የመገናኛ ብሀን ሲዘገብ ቆይቷል።


በ1997 ምርጫ ወቅት የአንድ ብሄር አባላት በገዢው ፓርቲ ህወሀት  ራስን የመጠበቂያ መሳሪያ እንዲታደላቸው መደረጉ በስፋት መዘገቡ ይታወቃል።

የፌደራል አቃቢ ህግ በቀድሞው የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋ/ዳይሬክተር መላኩ ፋንታ መዝገብ ላይ ባቀረበው ክስ፣ በህወሀቱ አባል ምክትል ዳይሬክተሩር አቶ ገብረዋህድ ወ/ጊዮርጊስ መኖሪያ ቤት ውስጥ 2 ታጣፊና ባለእግር ክላሾች፣ 4 ማካሮቭ ሽጉጦች፣ 2 ኮልት ሽጉጦች፣እና አንድ ስታር ሽጉጥ በድምሩ 9 የጦር መሳሪያዎች መገኘቱን ጠቅሷል።በሌላው የህወሀት አባል በ24ኛው ተከሳሽ በቀድሞው የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት አማካሪ በነበሩት በአቶ ወልደስላሴ /ሚካኤል ቤት ደግሞ 2 ባለሰደፍና ታጣፊ ጠመንጃዎች፣ አንድ ኡዚ ጠመንጃ፣ አንድ እስታር ሽጉጥ፣ አንድ የጭስ ቦንብ እና የተለያዩ ጥይቶችን ይዞ መገኘቱ ተገልጿል።

ግለሰቡ ከቀድሞው ጠ/ሚ አቶ መለስ ዜናዊ ባለቤት ወ/ሮ አዜብ መስፍን ጋር የጠበቀ ቁርኝት እንዳላቸው  በተቃራኒው ደግሞ ከደህንነት ሚኒስትሩ ከአቶ ጌታቸው አሰፋ ጋር በተፈጠረው አለመግባባት ለእስር መዳረጋቸው በተለያዩ የመገናኛ ብዙሀን ሲዘግብ ቆይተዋል።

 በተመሳሳይ ሴና ዋና ዳይሬክተሩ አቶ መላኩ ፋንታ ባለትዳር በማማገጥ ወንጀል አቃቢ ህግ ክስ እንደመሰረተባቸው ሰንደቅ ጋዜጣ ዘግባል። ዐቃቤ ህግ  አቶ መላኩ የስራ ኃላፊነታቸውን በመጠቀም ለስራ ጉዳይ የመጣችን ሴት፤ ትዳሯን ፈታና በትዳር ውስጥ ያፈራቻቸውን ሦስት ልጆች በትና አብራቸው እንድትሆን አድርገዋል ሲል ስልጣንን ያለአግባብ የመጠቀም የሙስና ወንጀል ፈፅመዋል ብሎአል።  ሰንደቅ አቃቢ ህግን ጠቅሶ እንደዘገበው ” ወ/ሮ መቅደስ ለማ የተባሉት እኚሁ ሴት የቀድሞ ባለቤታቸውን ንብረት የሆነውን ሳንክቸሪ ኢንተርናሽናል ኃ/የተወሰነ የግል ማህበር በ2001 ዓ.ም የስራ ግብር ለመክፈል ወደገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ሲሄዱ 144 ሺህ ብር እንዲከፍሉ በመጠየቃቸውና በዚህም ምክንያት አቤቱታ ለማቅረብ ወደ ምስራቅ አዲስ አበባ ቅርንጫፍ ለአንድ አመት ከ4 ወር መጉላላታቸውን ለማስረዳትና መፍትሄ ለማግኘት ወ/ሮ መቅደስ ለማ የአቤቱታ ደብዳቤ ይዘው ወደተከሳሹ ዘንድ በቀረቡበት ወቅት የፍቅር ግንኙነት” ጀምረዋል።  ተከሳሽ የነበረውን ስልጣን መከታ በማድረግ ባለጉዳዩዋ ቀደም ሲል ከከፈሉት ብር ውስጥ አንድ መቶ ሺህ ብር ተመላሽ እንዲሆን አድርጓል፤ በትዳር ውስጥ ያለችን ሴትም አማግጧል ሲል አቃቢ ህግ ክስ አሰምቷል።

ዐቃቤ ህግ ተከሳሽ “በጋብቻ ውስጥ ያለችን ሴት በመንግስት ተሽከርካሪና ነዳጅ ደብረ ሊባኖስ ገዳም ክብረ በዓል ላይ እንድትገኝ ከማድረጉም በላይ ቀኑ በውል ባልታወቀበት ዕለትም፤ በጋብቻ ውስጥ የነበረችው መቅደስ ለማን በግል ሾፌሩ አማካኝነት ወደ ባህርዳር ከተማ እንድትሄድ በማድረግ ሰመርላንድ ሆቴል ለአንድ ሳምንት አብረው እያደሩ እና በሾፌሩ አማካኝነት ከተማ ውስጥ እንድትዝናና ” አድርጋል ብሎአል።

አቃቢ ህግ ባቀረባቸው በርካታ የወንጀል ዝርዝሮች ውስጥ የሼክ ሙሀመድ ሁሴን አላሙዲንና በጄኔራል ክንፈ ዳኘው የሚመራው በመከላከያ ውስጥ የሚገኘው የብረታ ብረት ኮርፖሬሽን እቃዎች ያለቀረጥ እንዲገባላቸው ቢደረግም፣ ሌሎች ኩባንያዎች ሲከሰሱ ሁለቱ ድርጅቶች እና የኩባንያው መሪዎች አልተከሰሱም። አቃቢ ህግ እነዚህ ሁለት ግዙፍ ኩባንያዎች በሙስናው ውስጥ እንዳሉበት መረጃ ቢኖረውም ለመክሰስ ለምን ፈቃደኛ እንዳልሆነ አልታወቀም።

በቤይሩት ኢትዮጵያዊቷ በመኪና አደጋ ህይወትዋ አለፈ

       

የቆንስላ ጽፈት ቤቱ ሀላፊዎች በእህቶቻችንን ላይ የሚደርሰውን ግፍና መከራ ችላ በማለት የራሳቸውን ብቻ ቢዝነስ ሲያሳዱ የበርካቶች ህይወት እንደቀልድ ያልፋል: : ፥ ቤተሰቦቻቸው ተበድረው የላኳቸው ሊጆቻቸውን እሬሳ እንደገና በብድር ሲያስገቡት ብታዮ ልብ ይሰብራል:: ከዚህ በላይ በዜጎቹ ላይ ቁማር የሚጫወት የዜጎቹ መከራ ግፍ ስካይና ጉዳት የማያሳስበው መንግስት በሀለም ላይ አለ ?

.ከልብ ሀዘን ተሰምቶናል ቆንስላው ስራው ምን ይሆን? መንግስት ስራው ምን ይሆን?
11

Tuesday, October 22, 2013

በደም በተበከሉ እጆችና በወንጀለኞች የምትመራ አገር


አበራ ሽፈራው /ከጀርመን/
ዛሬ ይኸንን ፅሑፍ እንድጽፍ ያነሳሳኝ ጉዳይ አንድ ነገር ነው። ይኸውም አቶ ገብረምድህን አርዓያ ከአውስትራሊያ በኢትዮጵያ አቆጣጠር መስከረም 6 ቀን 2006 በተጻፈውና “የህወሓት ፀረ ኢትዮጵያ አካሄድና ዓላማ በመቃወም የሕይወት መሰዋዕትነት የከፈሉ አመራር ነበሩ ወይ? ከነበሩስ እነማን ናቸው?“ የሚለውንና በኢንተርኔት የተለቀቀውን ጽሁፍ ካነበብኩኝ በኃላ በርግጥም የህወሓት መሪዎች ምን ያህል የክፉ መንፈስ ፈረሶች መሆናቸውን ከጽሁፉ ከተረዳሁ በኃላ  ይህንን መጻፍ ግድ አለኝ።
የጽሁፉ ቁም ነገር በተለይም በኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት፣ የአማራው ህዝብ የትግራይ ህዝብ ጠላት አይደለም ይህ በውሸት አማራን ለማጥቃት የተፈበረከ ታሪክ ነው፣ ኤርትራ የአማራው /ኢትዮጵያ/ ቅን ግዛት ናት የሚለው ቅንጣት ታህል ሃቅነት የሌለው እናንት አመራር የፈጣችሁት የተገንጣይ ዓላማ ነው፣ ትግራይ የአማራ ቅኝ ግዛት ናት ማለት የአዕምሮ ድህነት ጠባብ ዘረኝነት ነው፤ ስለዚህም መወገዝ አለበት፣ ተሓህት የኢትዮጵያን ጥንታዊና ታሪካዊ ግዛትዋን እና ባህር በሯን የሚያስነጥቅ ፕሮግራም ነው፣ እና ሌሎች ሃሳቦችን ባነሱ ታጋዮችና በዛሬዎቹ መሪዎች መሃል የነበረን ሁኔታንና ፤ብዙዎች በዚህ የተነሳ ለሞት የተዳረጉ መሆኑንና፤ ዛሬ የአገራችን መሪዎች ሆነው የሚመሩን ምን ያህል ዘግናኝ ግድያዎችን አብረዋቸው በታገሉ ላይ የወሰዱትን አረሜናዊ ጭፍጨፋንም ያትታል። ከዚህም ጋር ተያይዞ እነዚህ ለኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት፣ ለህዝቦች እኩልነት የታገሉት ሃይሎች የከፈሉትንም መሰዋዕትነት ያትታል።  ሃገሬ የሞተልሽ ሳይሆን የገደለሽ በላ” ።
አስቀድሞም ቢሆን ኢትዮጵያዊነት ስነምግባርና አስተዳደግም የጐደላቸው ፤የስነልቦናና የበታችነት ሥሜት ሁሌ የሚፈታተናቸው ፤ለዓመታትም በፍርሓት ከመዋጣቸው የተነሳ ያገኙትን ሁሉ አብሮአቸውም የበላውንም ፣አብሮ አደጐቻቸውንም በየምክንያቱ የገደሉ መሆናቸውን ከጽሁፉ ተረድቻለሁ ።
ፈሪ በጩኸት ብቻ በርግጐ የመቃብሩን ግዜ ያፋጥናል ይኽንንም ከጨካኙ መሪያቸው ሞት በቀላሉ ለመረዳት ችያለሁ። አሁንም የሚታየው እውነት እንደሚያሳየው አዲስ አበባ ወጥተው የሚጮሁትን ፈርተው እየደጋገሙ የፍርሓት ዛቻ ሲያዘንቡባቸው ይሰማሉ፤ አንዳንዶችንም ይመታሉ ፣ያስራሉ፣ የሚፈልጉትን ሁሉ ያደርጉባቸዋል። ከዚህ ድርጊታቸው ስንነሳ አሁን እየፈጸሙ ያሉት ድርጊት ቀድሞውንም ሲፈጽሙት የነበረና አሁንም ያለቀቃቸው መሆኑን ስመለከት ህወሓቶች ኢትዮጵያዊ ስነምግባርና አስተዳደግ የጐደላቸው ፣ በክፋታዊ አስተሳሰባቸው የተበረዙ፤ የሌሎች ጭቁን ህዝቦችን ህልውና እየተዳፈሩ እነሱ ብቻ ነፃ አውጭ እነሱ ብሎ ነፃ አውጭ፤ ሌላው ለራሱ ነፃ መውጣት የማይታገልና እነሱ ባዘጋጁት የክፋት መዋቅር ውስጥ ለሁሌም እየገዙት የሚኖሩ የሚመስላቸው፤ እነሱ ለዚህ ክፋታዊ ግባቸው እንደታገሉ ሁሉ ለእውነተኛው ነጻነትማ ህዝቡ ለምን አይታገላቸው?
ህወሓቶች እጅግ በታሪክም፣ በሰውምና በአምላክም ፊት የ39 አመታት የወጀለኝነት ዶሴዎች ጥርቅም በፊታቸው ያለ መሆናቸውን የተረዳሁበት እጅግ መራራ ጽሁፍ ነበር ያነበብኩት ።
ብዙዎቹ አሁን አገሪቷን የሚመሩት የህወሓት አመርሮችና የተወሰኑት አባላት በሙሉ አብረዋቸው ለትግል የውጡትን ሰዎች እየጨረሱ ለዛሬ የደረሱ መሆኑንና እንቅልፍ የሌላቸው መሆኑን በቀላሉ ተረድቻለሁ። ከዚህ ጽሁፍ ተነስቼና ላለፉትም 22 አመታት በአጠቃላይ በኢትዮጵያና በምስራቅ አፍሪካ አካባቢ ከህወሓቶች አሸባሪነት ጋር ተያይዞ ህወሓቶች በግለሰቦች ፣በቡድኖች፣ በአገርና በአለም አቀፍ ፍርድ ቤቶች እንዲሁም ፍጹም ቅን ፈራጅ በሆነው በአምላክ ፊት ብዙ የወንጀለኝነት የወንጀሉም ክብደት ደግሞ በሰው ልጅ ግድያና በዘር ማጥፋት ወንጀሎች የሚጠየቁበት ሰፊ ምስረጃዎች በአገር ቤት በግለሰቦች፣በቡድኖች፣በጓደኞቻቸው በአብሮ አደጐቻቸው፣በአካባቢያቸው ሰዎች ሳይቀር የሚፈለጉ መሆናቸውን ይበልጥ እንድረዳ ጽሁፋ አድርጐኛል።
በነገራችን ላይ “እግዚአብሔር የለም” ከሚሉ የፖለቲካ ፈላስፎች የተማሩትን ለመተግበር በሚጥሩ ህወሓቶች በሰው ልጅ ላይ ከዚህ በላይ ወንጀሎችን ቢፈጽሙ ምንም የተለየ ነገር አይጠበቅባቸውም፤እግዚአብሔር የለም ለሚሉ ሠይጣን ግን በእነሱ ውስጥ እንዲኖር ይገደዳሉ። ሰይጣን የመጀመሪያው ተግባሩ በአምላክ አምሳል የተፈጠረውን የሰው ልጅ ከአምላክ ያገኘውን ክብር  ማሳነስና ክብሩን መንካት ዋናው ተግባሩ ነው። ለዚህም ነው ይህንን የሰውን ክብር ለመመለስና የዲያብሎስን ሥራ ሊያፈርስ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ የተገለጠው።የሰውም ልጅ በአምላክ ፊት ትልቅ ክብር ያለው ከመሆኑም በላይ የክብሩ ማለትም የመንፈሱም ማደሪያም አድርጐታል። ይህ ከቡር ፍጡር ነው እንግዲህ ሁሌ በህወሓቶች ፊት እየቀለለ የሚገኘው።
ህወሓቶች ግን አምላክ የፈጠረውን ሰው እንደፈለጋቸው በማሰር፣ በመግረፍ፣ በመግደልና በማሳደድ ሰፋፊ ሰይጣናዊ ተግባራቸውን ይፈጽሙበታል። የሰው ልጅ በህወሓቶች ፊት እንደተዋረደ በማንም ፊት በአሁኑ ሰአት ሲዋረድ አናይም። ጊዜና ዘመን ቆጥሮ አምላክ ይመጣል ለሁሉም በጊዜው እንደዋጋቸው ይከፍላቸዋል። በእርግጥም የአምባገነኑ መሪያቸው ሞት ለዚህ ትልቅ ደውል ነበረ፤ መማር ለሚፈልጉና ወደአይምሮአቸው ለመመለስ ለሚፈልጉ ሁሉ፤ ካልሆነ ግን በነዚህ ዘመናት ላፈሰሱት የንጹሓንን ደም ከሰማይ ዋጋ አለውና ሁሌም ይህ ደም ይጮሃልና የነዚህ ጨካኞች ፍርድ በሰማይ ብቻ ሳይሆን በምድርም ማየትን እንድንጀምር በጨካኙ መሪያቸው ላይ አምላክ ሥራውን ጀምሯል፤ ይቀጥላል።
ወደ ዋናው ሃሳቤ ስመለስ በተለይም ሲፈልጉ አንጋፋ ሲፈልጉ ደግሞ አቦይ እያሉ የሚያመጻድቁት ትልቁ የክፋት ፈረስ ሥብሃት ነጋ፣ መለስ ዜናዊ፣ ስዩም መስፍን፣ አባይ ፀሃዮ የፈጸሟቸውን አረመናዊ ድርጊቶች በጣም በሚገርም መልኩ ተመልክቻቸዋለሁ። በእርግጥ ከነዚህ ውስጥ በቅርብ ከሆነውና እራሳችን ከሰማነው የአንዳቸውን የክፋት ማስረጃም እንደምሳሌ እንወሰድ። አቶ መለስ በሞቱ አካባቢና የኢሳት ረዲዮና ቴሌቪዥን ፕሮግራም ሁኔታውን ቀድሞ ባሳወቀ ሰሞን ይህ አብሮት የበላውና የጠጣው ስብሃት ነጋ ለኝህ መሪ የነበረው ንቀትና ግዴለሽነት ምን ያህል ሰውየው ለሰው ልጅ ምንም ክብር የማይሰጥና በምንም መለኪያ የወረደ ለመሆኑ ትልቅ ማስረጃ ነበር። ሰውየው አምላክ ቀደመው እንጂ ስብሓት ለመሪያቸው ሊተኛለት እንደማይፈልግ በትክክል ንግግሩ ሁሉ ያሳያል።
ካነበብኩት ጽሁፍ ላይ እንደ አቶ ገብረመድህን ምስክርነት ከሆነ እነዚህ እና ሌሎች በሽብር ተግባራቸው የሚታወቁት የህወሃት አመራሮችና  የተወሰኑ አባላቶቻቸው አብረዋቸው በትግል ወቅት የነበሩትንና የተማሩ የነበሩትን፣እውነተኛ አገር ወዳዶችን፣የፍትህና የነጻነት ጉዳይ ያሳስባቸው የነበሩትን፣ስውር አላማ የሌላቸውንና እውነተኛ ታጋዮች በእነዚህ ክፉዎች እየተገደሉ እንዳለቁ ማንበብና መስማት እጅግ ይከብዳል።
እነዚህ በደም የተበከሉ እጆች ያላቸው ሰዎች ለዓመታት በትግራይ ክልል ፣ በአማራና በሌሎች ክልሎች የገደሉአቸውና ያስገደሉአቸው የሰዎች ብዛት ቀላል ባይባልም ምን ያህል በሰው ልጅ የመኖር ተፈጥሮአዊና ህገመንግሥታዊ መብቶች ላይ ክፉኛ ጠላት እንደሆኑና በእነዚህ ሰዎች ውስጥ በነበረው የሰይጣን ተልዕኮ ብዙዎችን ወደመቃብር እንዲወርዱ አድርገዋል።
እነዚህ ሰዎች የሰው ልጅ ሆነው ተፈጥረው እንደነሱ እኩል የተፈጠረውን ሰው ሲገድሉ፣ ሲያሰቃዩና ሲያሳድዱ ቅንጣት ያህል የማይሰማቸው ከመሆኑም በላይብዙ አረመኔያዊ  ድርጊታቸውን ሊፈጽሙ የሚችሉ ብዙዎችንም ከዙሪያቸው ማሳደጋቸውና መፍጠራቸውን ሳስብ ህዝቡ ለመከላከል ካልቆረጠ ከባድ ፈተናከፊትም እንዳለ በግልጽ ያሳያል።
እነዚህ ነፍሰ ገዳዮች ዛሬም የሚጠማቸው ሰው የመግደል አባዜ አለቅ ብሎአቸው ንጹሃንን መግደልና ማስገደል ተያይዝውታል። ገዳዮች ህወሃቶች በግድና በቅስቅሳበወጣው ህዝብና ወታደሮች እየታጀቡ ይቀበራሉ፤ ከንቱ ድካም የምድር ሥርዓት ይኸም ከንቱ ነው እንዳለው ጠቢቡ ሰለሞን። በህወሓቶች ወይም በአጋዚዎችና በሌሎች የህወሓት ወታደሮች የተገደሉት ንጹሃን ግን ሲፈለግ  ሬሳውን ገንዘብ ከፍላችሁ ውሰዱና ቅበሩ የተባሉ በኢትዮጵያ ምድር ስንቶች አሉ ዋ ኢትዮጵያ ታዲያ በደም የተጨማለቁ እየመሩሽ እንዴት መፍትሔ ታገኝ? እንዴትስ ትፈወሺ?
እንደ አቶ ገብረመድህን አርዓያ ምስክርነት ከሆነ ገሠሠው አየለ፣አጋዚ ገሰሰ፣ ሙሴ መሃሪ ተክሌ፣ አጽበሃ ዳኘው፣ ዶ/ር አታክልት ቀጸላ እና ሌሎች አመራር የነበሩ ሰዎችና አባላቶቻቸው ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ለህዝቦች እኩልነት ያደረጉት ተጋድሎ ቀላል እንዳልነበረ ይገልጻሉ።
አንድ ነገር ያሳዝነኛል አገራችን በደም በተለወሱ እጆችና በወንጀለኞች የምትመራ አገር መሆኗንና የአገራችንም መከራ የእነዚህ ሰዎች የደም ጩኸት ውጤት ነው ብዮም እገምታለሁ። እነዚህ ሰዎች የገደሏቸው ሰዎች ደም ይጮሃል መልስንም ከአምላክ ይፈልጋል። ወደድንም ጠላንም በደም የተነከረ እጅ ባላቸው ሰዎች ፣ ለሰው ልጅ ምንም ክብር በሌላቸው ግለሰቦች፣እግዚአብሔር አለ ብለው በማያምኑና እምነት በሌላቸው ሰዎች ስብስብና ለ39 ዓመታት መጠነ ሰፊ ወንጀልን በፈጸሙ እየተመራን መሆናችን በአገሪቷ ላይ ትልቅ ፈተና ነው ብዮ አስባለሁ።
እንዚህ ቡድኖች ለኢትዮጵያ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ለሚመሩት የህወሓት/ኢህአዲግ ፓርቲና በተለይም ለትግራይም ህዝብ ሳይቀር ትልቅ ፈተና ሆነው ያሉ ፓርቲውንም ወደቤተሰባዊ ትሥሥር የቀየሩና የብዝበዛ መዋቅራቸው እጅግ የተጠናከረ በመሆኑ ለአገሪቷና ለህዝቧ ትልቅ ሸክም ሆነው ያሉ መሆናቸውን ሁሉም ሊረዳው ይገባል።
ለዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እውን አለመሆን ሚስጥሩ እነዚህ ሰዎች አሁን ካለቡት ትልቅ ፈተና የተንሳና ሊገጥማቸው የሚችለው የተጠያቂነት ሁኔታ በፍጹም ሥልጣናቸውን በሃይል እስካልተቀሙ ድረስና ወይም ለፈጸሙት ወንጀል ከለላ እስካላገኙ ድረስ በአገራችን ውስጥ መፍትሔ ይመጣል ብሎ ለሚያስብ ሁሉ ዛሬ መርዶ ልነግር እፈልጋለሁ።እነዚህ ገዳዮች በትግራይ ጨምሮ በሁሉም የአገራችን ህዝቦች የሚፈለጉ መሆናቸውና ወንጀለኞች በመሆናቸው ከስልጣናቸው ለመልቀቅ በፍጹምእንዳማይፈልጉ ሊታወቅ ይገባል። ለዚህ ሁኔታ መፍትሄ ለማስቀመጥ ሶስት ብቻ አማራጮች እንዳሉ ይታዩኛል።
  1. ወንጀለኝነታቸውን የሚያጠናክሩ መረጃዎችን ለማሰባሰብ የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ማዘጋጀትና በአለም አቀፍ ደረጃ ተከሰው ወደፍርድ እንዲቀርቡ የሚሆኑበትን ሁኔታ መፍጥርና ተገቢውን ፍርድ እንዲያገኙ ማድረግ።
  2. ተገቢውን ሃይል አደራጅቶ ለእነሱ የሚመጥን ትግልና መሰዋዕትነትን ከፍሎ ከአገሪቷ ላይና ከህዝቡ ላይ ለሁሌም ማንሳት።
  3.  ይቅር ሊባሉ የሚችሉበትን ዋስትና መስጠትና አገሪቷ ከዚህ በኃላ በሰላምና በፍቅር በጋራ የምንኖርበትን ሁኔታ መፍጠር እንዳለብን ይታየኛል። ይህ ካልሆነ አይምሮአቸው ቆሽሿልና ሊፈወስ አይችልም ምን አልባት አንዳንዶቹን አምላክ በምህረቱ ካልተገኛናቸው በስተቀር፤  እንዚህ ሁኔታዎች በሌሉበት ሁኔታ መግደላቸውንም ብዝበዛቸውንም አያቆሙም።
በቅርብ ደግሞ በአክራሪነት ሰበብ ቀደም ሲል ሲያጠቁት የነበረውን የማንኛውንም ሃይማኖት እንቅስቃሴ ለመገደብ ትልቅ ሥራ ጀምረዋል። የሥራ መለኪያቸውም የኃይማኖት አክራሪነት እንዳይፈጠር የሚያስችል ሁኔታ እንደሆነ አስመስለው መነፈሳዊውን እንቅስቃሴ ከኢትዮጵያ ለማጥፋት ሰፊ እቅዳቸውን መተግበር ጀምረዋል። ይህንንም ለመተግበር በስልኮች የሚደረግን ጥሪ ምንም ኃይማኖታዊ ይዘት እንዳይኖረው፣የሃይማኖት ሁኔታ አንዱ የሥራ መገምገሚያ ሊሆን እንደሆነና ሊተገበርም እንደሆነ ይሰማል እነዚህንና እና መሰል ነገሮችን በማድረግ በሃይማኖት ላይ የተቃጣም ሥራ ጀምረዋል። በነገራችን ላይ አክራሪነት ከአስተምሮቱ የሚነሳና ወደ ጽንፈኝነት የሚያዘነብል እንቅስቃሴ እንጅ ሁሉንም በዚህ መልኩ ፈርጆ በኢትዮጵያ ሃይማኖትን ለማዳከም የሚደረግ እንቅስቃሴ ሁሉ ይልቁንም ነገ የሚጐዳው እራሱን ህወሃትን እንደሚሆን እርግጠኛ ነኝ።
ቀደም ሲል በእግዚአብሔር ላይ ትልቁን ዘመቻ በአገራችን የተደረገ እንቅስቃሴ ነበረ ደርግም በዚህ አባዜ ተለክፎ እንደነበር ይታወሳል። በወቅቱ በተነሱ የሶሻሊስቶች አስተሳሰብ በ60 ዎቹ መጨረሻ ባሉ ፓርቲዎች አካባቢ አምላክ የለም በሚሉ ሃይሎች መካከል የተደረገው የደም መፋሰስ ይኸው አስተሳሰባቸው ባመጣባቸው መዘዝ የዲያብሎስ መፈንጫ በመሆን የመጣባቸው መዘዝና የአስተሳሰባቸው ውጤት እንጂ የፖለቲካ አስተሳሰብ ተደርጎ መወሰዱ አይዋጥልኝም። ምክንያቱም የሰላማዊ  ፖለቲካና እምነት መገለጫዎች አንዱ ለሰው  ልጅ ባለን ክብርና ፍቅር መጠን የሚገለጽ እንጂ በአስተሳሰብ ልዩነት ላይ ተነስቶ ሰውን መግደል እንዳልሆነ ሁሉም ያውቃል። ሰውን መግደል የክፉ ሃይማኖቶች አስተምሮቶች ውጤትና የክፉ ፖለቲካ አስተሳሰቦችና አስተምርኦቶች ውጤት እንጂ ሌላ ጉዳይ ነው ብዮ አላስብም።
እንደኔ አስተሳሰብ የሰው ልጅ ትልቅ ሥፍራ ሊሰጠው የሚገባውና በአምላክ መልክ የተፈጠረ ፍጡር መሆኑን አምናለሁ። ይህንን ሰውና እምነቱን ሊጐዳ የሚመጣ ኃይል ሁሉ መነሻው ፖለቲካ ሳይሆን ከፖለቲካው ጀርባ ያሉ የሠይጣን ተልዕኮ ውጤቶች ናቸው።
እንግዲህ እነዚህን ወንጀለኞች ማወቅ፣ መለየት፣ ማስረጃን ማሰባሰብ፣ ለዚህም የሚረዳ ድርጅት ማቋቋምና ወደ ሥራ መግባትና በፍርድ ፊት ማቅረብ ያለብን ጊዜ አሁን እንደሆነ አስባለሁ። ወገኖች እንዚህን ወንጀለኞች በሁሉም አቅጣጫ ታግሎ ማሸነፍና ለህግ ማቅረብ ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለምና ዛሬ እንነሳ።
ከአቶ ገብረምድህን አርአያ ብዙ ተምሬአለሁ፡፤ አገራችን አሁን የምትመራው በደም በተበከሉ እጆች ባላቸው ቡድኖች እጅ ነው። እነዚህ ሓይሎችን በትክክል መቃወም፣ ለፍርድ ለማቅረብ አስፈላጊውን ርብርቦሽ ማድረግና ከአገሪቷ ጫንቃ ላይ ማንሳት ለአገሪቷ ሰላም፣ ብልጽግናና የሰዎችንም እኩልነትና ሰላም ስለሚያረጋግጥ ልንነሳ ይገባል እላለሁ። በዚሁ አጋጣሚ ለአቶ ገድረመድህን አርዓያ ያለኝን ትልቅ አክብሮት ለመግለጽ እፈልጋለሁ። አሁንም ሌሎች መረጃዎችን ለህዝቡ በማቅረብ ማወቅ የሚገባው ህዝብ ሉለ እንዲያውቅ እንደሚያደርጉ ተስፋዮ ትልቅ ነው፤ በተለይም ጽሁፎችዎን በመጽሃፍ መልክ ለማውጣት ቢጥሩ ሰፊ አንባቢ ለማግኘት ይችላሉና እባክዎ ይበርቱ እላለሁ ። ቸር ይግጠመን።

ትእምት የህወሓት ንብረት እንጂ የትግራይ ህዝብ ሃብት እንዳልሆነ የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ ኣባልና የማረት ሓላፊ ኣቶ ተክለወይኒ ኣሰፋ ተናገሩ

!

ኣንድ
በ1993 ዓም የህወሓት ክፍፍል መለስ የነ ስየ/ተወልደ ቡድን ለማሸነፍ በህወሓት ሰነፎች (የራሳቸው ነፃ ሓሳብ ያልነበራቸው) የፓርቲው ሰዎች ኣሰባስቦ ‘እኔን መርጠዋል’ ብሎ በህወሓት ሊቀመንበርነቱና የጠቅላይ ሚኒስተር ስልጣኑ ይዞ እንደሚቆይ ኣሳወቀ። ኣቶ ኣባይ ወልዱም ይሄንን ‘የመለስ ራእይ’ (ሰነፎች ማሰባሰብ፣ ጎበዞች ማባረር) እየተገበረ ይገኛል።
ሰነፎቹ ስልጣን ተረካቢዎች ኣሁን የጠበቁት የህዝብ ድጋፍ ባለ ማግኘታቸው ግራ ተጋብተው የሚናገሩትን ነገር እስካለማወቅ ደርሰዋል። በተለይ ኣዜብ መስፍንና ኣባይ ወልዱ (እንዲሁም ስብሓት ነጋ) ለሚናገሩት ነገር ‘ይቅር’ እንበላቸው። ብቁ ፖለቲከኞች ኣለመሆናቸው እየነገሩን ነው። ጭንቀታቸው በኣደባብይ ሲናገሩ ያሳዝናሉ።
ሁለት
የህወሓት መሪዎች ከስልጣን መውረድ የማይፈልጉበት ምክንያት (1) እስካሁን የሰሩት ጥፋት እንዳይጋለጥ ይሰጋሉ። (2) የትእምትን ሃብት ማጣት ኣይፈልጉም። (3) ፓርቲው ስልጣን ከለቀቀ ልክ እንደ የድሮ የደርግ ባለስልጣናት በጠላትነት ተፈርጀው ከሀገር የሚባረሩ ይመስላቸዋል።
‘ትእምት ግን የማን ነው?’ ብለን ስንጠይቅ መልሱ ‘የህወሓት መሪዎች’ የሚል እንደሚሆን ግልፅ ነው። ባለፈው የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ ኣባልና የማረት ሓላፊ ኣቶ ተክለወይኒ ኣሰፋ ትእምት የህወሓት ንብረት እንጂ የትግራይ ህዝብ ሃብት እንዳልሆነ መናገሩ የሚገልፅ post ኣድርጌ ነበር። (መረጃው ያገኘሁት ከፌስቡክ ጓደኛየ ነበር)። መቼና የት እንደተናገረው መጥቀስ እንዳለብኝ ከጓደኞቼ ኣስተያየት ደርሶኛል።
ከተሰጡኝ ኣስተያየቶች በመነሳት ለማጣራት ስሞክር ተክለወይኒ ኣሰፋ ይሄን የተናገረው ባለፈው ዓመት ሮብ ሚያዝያ 10, 2004 ዓም ሲሆን ቦታው በMIT የስብሰባ ኣዳራሽ እንደነበር ለመረዳት ችያለሁ። ‘ለምን ያን እንዲናገር (ኣምኖ እንዲቀበል) ተገደደ?’ የሚለውን ጥያቄ መመለስ ተገቢ ነው፣ ምክንያቱም ብዙ ግዜ (ወይ ሁልግዜ) የህወሓት መሪዎች ትእምት የግል ሃብታቸው መሆኑ እያወቁ ለፖለቲካ ፍጆታ ሲባል ግን ‘ትእምት የህዝብ ነው’ ይሉን ነበር።
MIT (Mekelle Institute of Technology) ሲቋቋም ዓላማው የክልሉ ጎበዝ ተማሪዎች ተመጠው እዛው ተምረው ገዢውን ፓርቲ በታማኝነት እንዲያገለግሉ ታስቦ ነበር። ቁስ ነገር በመስጠት ጎበዝ ልጆችን ባርያ ኣድርጎ ለመግዛት፣ ይህንን ካልተቻለ ደግሞ ስርዓቱ እንዳይቃወሙ ለማድረግ ነ ው። ህወሓቶች ጎበዝ ተማሪዎችን (ወይ ሙሁራን ባጠቃላይ) ይፈራሉ። ምክንያቱም እነሱ በደምብ የሚያውቁት በሓሳብ ማሸነፍ ሳይሆን ተኩሶ መግደል ነው። ኣሁን የቸገራቸው ይሄንን ነው፤ (ውድድሩ በጠመንጃ ሳይሆን በሓሳብ መሆኑ)።
የMIT ተማሪዎች ግን ህወሓቶች እንደጠበቁት (ስለበሉ ስለጠጡ) ‘ታማኝ ኣገልጋዮች’ መሆን ኣልቻሉም። ጥያቄዎች ማንሳት፣ መብት መጠየቅ፣ መቃወም … ምናምን ጀመሩ። ማስተካከል እንዳለባቸው ተነገራቸው። ኣልተሳካም። ህወሓቶች በጉዳዩ ተሰብስበው ተወያዩ። ‘እነዚህ ተማሪዎች በራሳችን ገንዘብ ኣስተምረን ለኛ ጠላቶች እየፈጠርን ነን።’ (MIT fund የሚደረገው ከትእምት ነበር)። እንደዉጤቱም ‘ጠላቶች’ ለመፍጠር ገንዘባቸው ማባከን እንደሌለባቸው ተስማምተው የMIT ቡጀት ተዘግቶ ተቋሙ ወደ መቐለ ዩኒቨርስቲ እንዲጠቃለል (በጀቱ ከፌደራል መንግስት እንዲሆን ተወሰነ)።
ይሄን ዉሳኔ የMIT ማህበረሰብ ተቃወመው (በወቅቱ ስለ ጉዳዩ ፅፌ ነበር)። ብዙ ችግር ተፈጠረ። የህወሓት መሪዎች የMIT ማህበረሰብ (ተማሪዎችና ኣስተማሪዎች) እየሰበሰቡ ማነጋገር ተያያዙት ። ከነዚህ መሪዎች ኣንዱ ተክለወይኒ ኣሰፋ ነበር። እሱ ተማሪዎቹን ሰብስቦ በበጀት እጥረት ምክንያት MIT fund ማድረግ እንደማይችሉና የመቐለ ዩኒቨርስቲ ኣካል መሆን እንዳለበት ይነግሯቸዋል። ሰመረ የተባለ ተማሪ እጁን በማውጣት ‘ትእምት የትግራይ ህዝብ ሃብት ነው ትሉናላቹ ግን በትክክል የህዝብ ከሆነ ለምን ለህዝብ በሚጠቅም መልኩ ኣታውሉትም?’ ብሎ ይጠይቃል። ተክለወይኒም በጣም ተናዶ “ማን ኣለህ ዉሸታም! ትእምት (EFFORT) የህወሓት ነው፤ ህዝብ ደሞ ማነው?” (“መን ኢሉካ ሓሳዊ! ትእምት ናይ ህወሓት እዩ። ታይ እዩ ህዝቢ ኸ?” ብሎ መለሰለት።
ተክለወይኒ እንዲህ መናገሩ ምን ኣዲስ ነገር ኣለው? ኣዲስ ነገር ኣይደለም። ምናልባት ኣዲስ ከሆነ ግን በራሳቸው ኣንደበት በህዝብ ፊት መናገራቸው ብቻ ነው እንጂ የህወሓት መሆኑማ ማንም ሰው ያውቃል። ኣሁን ኣሁን እኮ ግን ትእምት የህወሓት ኣባላት መሆኑ ቀርተዋል። ትእምት የሁሉም ኣባላት ኣይደለም። ትእምት የተወሰኑ የህወሓት መሪዎች የግል ሃብት ነው። የጥቂት ሰዎች ነው።
ሦስት
በመኾኒ በሺዎች የሚቆጠሩ መኖርያ ቤቶች እንደሚፈርሱ በመንግስት ኣካላት ከተነገረ በኋላ ኗሪዎቹ ኣማራጭ መጠልያ እንዲዘጋጅላቸው ቢጠይቁም መፍትሔ እንዳላገኙ ጠቅሼ ነበር። ከዚህ በመነሳት “ቤቶቹ የሚፈርሱት በምን ምክንያት ነው?” የሚል ነገር ተነስተዋል። የሚፈርስበት ምክንያት “ሕገ ወጥ ግንባታ” ተብሎ ነው።
በመኾኒ ወደ 7 ሺ የሚጠጉ ቤቶች ‘ሕገ ወጥ’ ከሆኑ ‘ሕጋዊ የሆነ ቤት የለም’ ልንል ነው። ግን ይህን ሁሉ ቤት ‘በሕገውጥ መንገድ’ ሲገነባ (ለብዙ ዓመትም ኑሮበታል) ኣስተዳዳሪዎቹ (የመንግስት ተወካዮቹ ) የት ነበሩ? እስኪገነባ ድረስ ዝም ብለው እያዩ ነበር ወይስ ከተገነቡ በኃላ፣ ኣገልግሎት መስጠት ከጀመሩ በኋላ ነው ‘ሕገወጥ’ የሆኑት? ‘ሕገወጥ’ ቤት ከተገነባ ከጅምሩ ነው መቆም የነበረበት። ራሳቸው ይፈቅዳሉ፣ ይሰጣሉ፣ በኋላ ያፈርሳሉ። ይህንን ተግባር በነዋሪዎቹ የሚፈጥረው የስነ ልቦና ችግር ቀላል ኣይደለም። እንደዚህ ዓይነት ችግር ከመልካም ኣስተዳደር እጦት የሚመነጭ ነው።
የህወሓት መሪዎች ያዳላሉ። ምሳሌ ልስጣቹ፡ ከተወሰኑ ዓመታት በፊት በመቐለ ከተማ የመኖርያ ቤቶች ግንባታ ጉድ ነበር። ብዙ የከተማው ነዋሪዎች ‘ሰራዋት’ ተብሎ በሚጠራ ኣከባቢ (የከተማው ኣስተዳደር ፍቃድ ኣግኝተው፣ ማንም ሳይከለክላቸው) በሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶች ተገነቡ። ኣገልግሎት መስጠት ጀመሩ።
በተመሳሳይ መልኩ (በተመሳሳይ ግዜና ሁኔታ) ግን ለየት ባለ ቦታና ለየት ባሉ ሰዎች ሌላ ዓይነት ቤቶች (ቪላዎች) ይገነቡ ነበር። እነዚህ ለየት ባለ ቦታ የተገነቡ ቪላዎች Hill Top Hotel ኣከባቢ በሚገኝ ‘ልዩ መንደር’ ነው። ‘ልዩ መንደር’ ያልኩበት ምክንያት እዛ ኣከባቢ ቤት መስራት የሚፈቀድለት ሰው የህወሓት ከፍተኛ ባለስልጣን መሆን ኣለበት። ሌላ ተራ ሰው እዛ ኣከባቢ ቤት መስራት ኣይፈቀድለትም። በወቅጡ የነበረ “ጥሕሎ” የተሰኘ መፅሔት “ኣፓርታይድ መንደር” ብሎ ሰይሞታል። እስካሁንም “ኣፓርታይድ መንደር” ተብሎ ይጠራል። ባለስልጣናቱ ለብቻቸው ተለይተው የሚኖሩበት ሠፈር ስለሆነ ነው።
ሁለቱም የ’ሰራዋት’ (የሰላማዊ ሰው)ና ‘ኣፓርታይድ መንደር’ (የባለስልጣናቱ) የቤት ግንባታዎች ማንሳት ለምን ኣስፈለገ? በሰራዋት የተገነቡ ቤቶች ሁሉም በግፍ (በዶዘሮች) እንዲፈርሱ ሲደረግ የባለስልጣናቱ (ኣፓርታይድ መንደር) ግን ማንም ሳይነካው እስከኣሁን ድረስ ኣለ። የተራ ህዝብ ፈረሰ (ሕገወጥ ተባለ) የራሳቸው (የባለስልጣናቱ) ግን ‘ሕጋዊ ሆነ’ (ምክንያቱም እነሱ ኮ ከሕግ በላይ ናቸው)።

ሌባ ተይዞ ዱላ ይጠየቃል? በሆላንድ


መስፍን ወልደ ማርያም
ጥቅምት 2006
በአሥራ አምስተኛው  ምዕተ-ዓመት ግድም ሆላንድ የታወቀ የባሕር ኃይል ሆኖ ከደቡብ አፍሪካ እስከደቡብ አሜሪካ፣ የኔዘርላንድ የቆዳ ስፋት 41 526 ኪሜ ካሬ ወይም የትግራይ ግማሽ ነው፤ የሕዝቡም ቁጥር አሥራ ስድስት ሚልዮን ተኩል አይሞላም፤ የትግራይን ግማሽ በሚሆን መሬት ላይ የትግራይን ሦስት እጥፍ ግድም የሚያህሉ ሰዎች ይኖሩበታል፤ ሆኖም ጥንት ከደቡብ አፍሪካ እሰከደቡብ አሜሪካ፣ በእስያም ኢንዶኒዝያ ላይ የቅኝ ግዛት የዘረጋ ትንሽ አገር ነበር፤ አሁንም ትንሽ አገር ነው፤ አሁንም ሀብታም አገር ነው፤ ዋናው ሀብቱ ሕዝቡ ነው፤ አሥራ አምስት ሚልዮን ግድም የሚሆን ሕዝብ ከባሕር ጋር እየታገለ ያገኘውን መሬት ይዞ እንዲህ ያለ ሀብታም መሆኑን ሳይ እኛ በጣም ሰፊ መሬትና ስድስት ጊዜ ያህል ከኔዘርላንድ የሚበዛ ሕዝብ እያለን ቆሞ-ቀር ብቻ ሳይሆን ወደኋላ መገስገሳችን ሳይሻክረኝ አልቀረም።
ኔዘርላንድ በከፊል በባሕር ተሸፍኖ የነበረ ነው፤ በሰው ኃይልና በሰው ጥበብ ባሕሩ ተገፍቶና ተገድቦ መሬቱ ለጥቅም እንዲውል ተደርጓል፤ በዓለም ውስጥ እንደኔዘርላንድ ከባሕር ጋር ታግሎ ያሸነፈና ከባሕር ጠለል በታች የነበረውንና ረግረጉን መሬት ለጥቅም ያዋለ አገር የለም፤ በተለይ የሰሜኑ ክፍል ከባሕር የወጣ መሬት ነው።
በኔዘርላንድ ገጠርና ከተማ እየገጠሙ ናቸው፤ በየመንገዱ ላይ እርሻ፣ ላሞችና በጎች፣ አንዲሁም ፈረሶች ሲግጡ ይታያሉ፤ እዚህ ከባሕር ጋር እየታገሉ ባወጡት መሬት ላይ ቤታቸውንም ሆነ እርሻቸውን በፈለጉት ሁኔታ መጠቀም ይችላሉ።
ኔዘርላንድ በዴሞክራሲያዊ የዘውድ መንግሥት የሚተዳደር አገር ነው፤ በቅርቡ የኔዘርላንድ ንግሥት ዕድሜያቸው ስለገፋ ዘውዱን ለልጃቸው አስረክበው እሳቸው በክብር እቤታቸው ወይም እግቢያቸው ውለዋል፤ በኔዘርላንድ የመብት ጉዳይ ዋና ሥፍራን የሚይዝ ነው፤ በአምስተርዳም ከተማ ከሚኖር ከአንድ ወዳጄ ጋር ስንጫዋወት በኢትዮጵያ አንገብጋቢ ጉዳይ ስለሆነው ስለፍትሕ ጉዳይ አነሣሁ፤ በዚሁ ላይ እንዳለን አንድ ታሪክ ነገረኝ፤ በዚሁ አገር አንድ ቤተሰብ አገር ሰላም ብለው ተኝተዋል፤ ድንገት ስልክ ይደወልና የቤት እመቤቲቱ ስልኩን ለመመለስ ወደሳሎን ስትገባ የሳሎኑ በር ተከፍቶ ታያለች፤  ሁኔታው ቀፈፋትና ዘወር ስትል አንድ ጎረቤት የሆነ ሰው የእስዋን ቴሌቪዥን ይዞ እንደቆመ ዓይን ለዓይን ይጋጠማሉ፤ እየተርበደበደች ለፖሊስ ስልክ ስትደውል ጎረቤትዋ ቴሌቪዥኑን እንደያዘ ከሴትዋ ቤት ወጥቶ ወደራሱ ቤት ይገባና በሩን ቆልፎ መብራቱን አጥፍቶ ይቀመጣል።
የተጠሩት ፖሊሶች ይመጣሉ፤ ሴቲቱ የደረሰባትን ትናገርና የ‹‹ሌባው››ን ቤት እያሳየች አሁን ብትገቡ ቴሌቪዥኔን ታገኛላችሁ ትላቸዋች፤  አስቲ ቴሌቪዥኑን የገዛሽበትን ደረሰኝ አሳዪን ይላሉ፤ ደረሰኝ የላትም፤ የቴሌቪዥኑን መለያ ቁጥር ይጠይቃሉ፤ ያንንም አታውቀውም፤ ፖሊሶቹ ግራ ተጋብተው ታዲያ ሰውዬውን ከመኝታው አስነሥተንና በሩን አስከፍተን ምን አድርግ ልንለው ነው፤ እዚያ ቤት ውስጥ ያለው ቴሌቪዥን የአንቺ ለመሆኑ ምንም ማስረጃ ስለሌለሽ ሰውዬውን አናሸብረውም ብለዋት ሄዱ! ይህ ትምህርት ይሆነዋል፤ ይገባዋል፤ ለምትሉት ሰው፣ በተለይ ሕግ አስከባሪ ነው ለምትሉት ንገሩ!
በዚህ ታሪክ ስደነቅ ሌላ አስደናቂ ታሪክ ነገረኝ፤ አንድ ወሮ-በላ ቢጤ አንድ ቤት ውስጥ በቀዳዳ ገብቶ ተኝቶአል፤ የቤቱ እመቤት ልታስወጣው ብትሞክር አልቻለችም፤ ቢቸግራት ለባልዋ ትነግራለች፤ አበሻ ባልዋ ይሄድና ሰውዬውን አስወጥቶ ሁለተኛ እዚህ ብትመጣ እጅህን እቆርጠዋለሁ፤ ይለዋል፤ከጥቂት ጊዜ በኋላ ባለቤቱ የቤቱን በር ደወል ሰምቶ ሲከፍት ፖሊሶች ያያል፤ ከፖሊሶቹ ጋር ቀደም ሲል እጅህን እቆርጠዋለሁ የተባለው ሰው ቆሞአል፤ ፖሊሶቹ እጅህን እቆርጥሃለሁ ያለው እሱ መሆኑን ካረጋገጡ በኋላ ሰውዬው በዛቻው እንደተጨነቀና የዚህም ጭንቀት ምክንያት አንተ ነህ፤ ሰውዬውን አስሸበርከው! በማለት ማስፈራራቱ ማሰቃየት እንደሆነ አስረድተው እንዳይደግምህ ይሉትና ለመሆኑ ከየት ነው የመጣኸው ብለው ይጠይቁታል፤ ከአፍሪካ ሲላቸው አፍሪካ ሂድና እጅ እቆርጣለሁ እያልህ አስፈራራ፤ እዚህ ግን እንዲህ ማለት አይቻልም፤ ብለውት ይሄዳሉ፤ መለስ ዜናዊ ጣታችሁን እንቆርጣለን፤ እጃችሁን እንቆርጣለን፤ እያለ በሕዝብ ምክር ቤት ሲናገር ሁላችንም ሰምተናል፤ እሱ አሸባሪ ሳይባል እኛም ተሸበርን ብለን የምንጮህበት ሳናገኝ ተላልፈናል።
በኔዘርላንድ አንዳንድ ቦግ ብለው የሚታዩ ነገሮች አሉ፤ ለምሳሌ መንገዶቻቸው በጣም ግሩም ናቸው፤ ለቢስክሌት ልዩና ራሱን የቻለ መንገድ አላቸው፤  በኔዘርላንድ የባህል ጭቆና የሚባል ነገር የለም፤ እንዲያውም የባህል ጭቆናን የሚሽር ባህል እየገነቡ ናቸው ለማለት ይቻላል፤ እኛ የባህል ባሪያዎች ሆነን እንኖራለን፤ ብዙ ኢትዮጵያውያን ባይስማሙበትም የመክሸፋችን ዋና ምክንያት ተጨቁነን ጭቆናን አክባሪዎች መሆናችን ነው፤ የችግራችን ሁሉ መሠረት ይህ ክፉ ባህል ነው።

Saturday, October 12, 2013

የአቶ ዳውድ ኢብሳ ባለቤት አረፉ

የአቶ ዳውድ ኢብሳ ባለቤት ወ/ሮ ሴና ትናንት ምሽት ኖርዌይ በሚገኝ የስደተኛ መጠለያ ውስጥ ማረፋቸው ተሰማ። ወ/ሮ ሴና ላለፉት 20 አመታት ኤርትራ ውስጥ የነበሩ ሲሆን እዚያ በደምግፊት ህመም ይሰቃዩ እንደነበርም ኖርዌይ የሚገኝ ምንጫችን ገልጾልናል።
ምንጫችን እንደገለጸልን ከሆነ ወይዘሮዋ ኖርዌይ ከመግባታቸው በፊት እውነተኛ ስማቸውን በመቀየር በስዊድን የፖለቲካ ጥገኝነት ጠይቀው ነበር። ስማቸውን ለመቀየር የተገደዱበትም ምክንያት የአቶ ዳውድ ኢብሳ ባለቤት መሆናቸው ቢታወቅ ትግሉን ሊጎዳ ይችላል በሚል ሂሳብ መሆኑ ነው።
የስዊድን  መንግስት የጥገኝነት ጥያቄያቸውን ውድቅ በማድረጉ ወይዘሮዋ ወደ ኖርዌይ በመግባት እዚያው እንደገና የፖለቲካ ጥገኝነት ይጠይቃሉ።  ይሁንና የአሻራ ምርመራቸው ሲጣራ ስዊድን ጥገኝነት ጠይቀው እንደነበር በማሳየቱ፡ የኖርዌይ መንግስትም ጥያቄያቸውን ውድቅ አደረገ።  በዚህ መሃል የወይዘሮዋ  የደምግፊት ህመም ጠንቶ፡ ከዚህ አለምበሞት መለየታቸው ታውቋል። ነብስ ይማር። ለቤተሰቦቻቸውም ጽናቱን ይስጣቸው።