የኢትዮጵያ ህዝብና እናስተዳድረዋለን የሚሉት አምባገነን ገዢዎቹ ተስማምተውና አንዱ ሌላውን አክብሮ የኖረበት አንድም የታሪክ አጋጣሚ የለም። የእስከዛሬው ታሪካችን ምዕራፍ በጥቅሉ ሲታይ ታሪካችን የሚቋጨው ህዝብ ተረገጠ፤ ተጋዘ፤ ገዢዎች ደግሞ ረገጡ፤ ገዙ፤ አሰሩ፤ አጋዙ እየተባለ ነው።

አዎ! የኢትዮጵያ ህዝብ እስከዛሬ ባለው ታሪኩ ተግዟል፤ ተረግጧል፤ ተንቋል፤ ተንቋሿል። የዘንድሮው በተለይ ባለፉት ሁለትና ሦስት ሳምንታት እየደረሰብን ያለው ብሄራዊ ውርደትና ንቀት ግን ታይቶም ተሰምቶም የማይታወቅ ልዩ ከልዩም ልዩ ነው። በቀዳማዊ ኃ/ሥላሤ ዘመን የኢትዮጵያ ህዝብ ልክ እንደዛሬው ሰብዓዊ መብቱ ተረግጧል፤ ፍትህ ተነፍጓል፤ ነጻነቱን ተገፍፏል፤ ሆኖም አገር ውስጥም ከአገር ውጭም ፈላጊና ባለቤት አንደሌለው የቤት ውስጥ እንስሳ የወገንም የባዳም እጅ አልተረባረበበትም። አንገፍግፎን አንፈልግም በቃ ብለን ያስወገድነው የቀዳማዊ ኃ/ሥላሤ ስርዐት በስልጣን ላይ በነበረበት ግዜ “ኢትዮጵያ” የሚለው ስምና “ኢትዮጵያዊነት” አገር ውስጥም ሆነ አውሮፓ፤ አሜሪካና አፍሪካ ውስጥ እጅግ በጣም የተወደደና የተከበረ ስም ነበር።
ዛሬ ወያኔ ነጻ አወጣኋችሁ፤ እኩልነት አመጣሁላችሁ እያለ በሚሰብክበት ዘመን ግን የኢትዮጵያ ሀዝብ አገር ውስጥም በውጭ አገሮችም ባለቤት አንደሌለው ፈረስ ማንም የሚጋልብበት ፈላጊ እንደሌለው ዕቃ ያገኘ ሁሉ እንዳሰኘው እጁን የሚያሳርፍበት የተናቀ ሀዝብ ሆኗል። ለመሆኑ ለምንድነው ኢትዮጵያዊነት እንደዚህ እንደ ተራ ዕቃ የቀለለው? ኢትዮጵያውያንስ ለምንድነው በየሄዱበት እንዲህ አይነት ውርደትና ስቃይ የሚደርስባቸው? መልሱ ቀላል ነው። “ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ” ወይም “ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ ባለዕዳ አይቀበለውም” ነው።
የወያኔ አገዛዝ እኛ ኢትዮጵያውያን “ኢትዮጵያዊነት” እያልን ስለምንሳሳለትና ስለምንከባከብለት ትልቅና ክቡር ሀሳብ በፍጹም ግድ የለውም። እንዲያውም ወያኔ ሽንጡን ገትሮ ከሚታገላቸው ዋና ዋና ብሄራዊ እሴቶቻችን ውስጥ “ኢትዮጵያዊነት” የመጀመሪያው ነው። ስለዚህም ነው ባለፉት ሃያ ሁለት አመታት በግልጽ እንደተመለከትነው “ኢትዮጵያዊነት” ብለው የተጣሩ፤ የጮሁ፤ ህዝብን ያስተማሩና የታገሉ ግለሰቦች በወያኔ እየተለቀሙ የታሰሩትና የተገደሉት። ከአገር ውጭም ቢሆን በየውጭ አገሩ የሚገኙት የወያኔ ኤምባሲዎች ኢትዮጵያውያን ከአገራቸው ውጭ ማግኘት የሚገባቸውን የዜግነት አገልግሎት የሚሰጡት ዜግነታቸውን እያዩ ሳይሆን ቦንድ የገዛ ያልገዛ፤ “ልማታዊውን መንግስት” የደገፈ ያልደገፈ እያሉ ወይም “የወርቃማው ዘር” አባልነቱን እያጣሩ ነው።
እነዚህንና ሌሎችም እነዚህን የመሳሰሉ ሰንካላ የወያኔ መስፈርቶች ያላሟሉ ኢትዮጵያውያን አገር ውስጥም ከአገር ውጭም ወያኔ በዜግነት ሳይሆነ በጠላትነት የሚመለከታቸው ሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃ ዜጎች ናቸው። ዛሬ ከአፍሪካ፤ ከኢሲያና ከላቲን አሜሪካ አገሮች ስራ ፍለጋ ሳዑዲ አረቢያ ከሄዱ ዜጎች ውስጥ እንደ ኢትዮጵውያን እጁንና እግሩን ታስሮ የተገረፈ፤ እንደሴቶቻችን በሳዑዲ ጎረምሶች የተደፈረና እንደ ኢትዮጵውያን በየአደባባዩ የተገደለ የሌላ አገር ዜጋ የለም። ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ የሚገኙ የሌሎች አገሮች ኤምባሲዎች የዜጎቻቸው መብት በሳዑዲ መንግስትና ህዝብ ሲደፈር ለምን ብለው ይጠይቃሉ ወይም ለዜጎቻቸው ግዜያዊ መጠለያ፤ የህክምና እርዳታና የህግ ሽፋን ይሰጣሉ እንጂ ኤምባሲያቸው በራፍ ላይ “ዝግ ነው” የሚል ጽሁፍ አይለጥፉም።
የወያኔ ኤምባሲ ግን ከስረ መሠረቱ የተቋቋመው የወያኔን የራሱን እንጂ የኢትዮጵያን ህዝብ ጥቅም ለማስጠበቅ ስላልሆነ ይህንን የሌሎች አገሮች ኤምባሲዎች ለዜጎቻቸው የሚያደርጉትን ጥበቃና እንክብካቤ ለወገኖቹ ለማድረግ አልታደለም፤ ፍላጎቱም የለውም። ይህንን ቅሌትና ውርደት ደግሞ ባለፉት ሁለትና ሦስት ሳምንታት በግልጽ ተመልክተናል። ጂዳና ሪያድ ውስጥ በዜጎቻችን ላይ የሚደርሰውን መከራና በደል ተቃውመው ሠልፍ የወጡ ኢትዮጵያውያን በሳዑዲ ፖሊሶች ታድነው እንደታሰሩ ሁሉ አዲስ አበባ ውስጥም በወንድሞቻችንና እህቶቻች ላይ እንዴት እንዲህ አይነት በደል ይፈፀማል ብለው ሳዑዲ ኤምባሲ ፊት ለፊት ሠላማዊ ሠልፍ የወጡ ኢትዮጵያውያን በአረመኔዎቹ የወያኔ ፖሊሶች ታድነው ታስረዋል፤ተደብድበዋል። አዎ! ኢትዮጵያውያን ሳዑዲ ውስጥም ኢትዮጵያ ውስጥም ለምን የሳዑዲን መንግስት ተቃወማችሁ ተብለው በሁለቱም አገር ፖሊሶች እየታደኑ ታስረዋል ተደብድበዋል።
ከወያኔና ከጥቂት ሆድ አምላኪ ደጋፊዎቹ ውጭ በአገር ውስጥና በመላው ዓለም የሚገኘው ኢትዮጵያዊ በአንድ አላማ ዙሪያ የተሰባሰበበትና አንድ ሳምንት ሙሉ አንድ ቃል በአንድ ትንፋሽ የተነፈሰበት ግዜ ቢኖር ወርሃ ህዳር 2006 የመጀመረያው ነው ማለት ይቻላል። የአንድ አገር ህዝብ በአንድ አላማ ስር ሲሰባሰብና በአንድነት ሲቆም ከማንም ከምንም በላይ በዚህ አንድነት መጠቀምም መደሰትም ያለበት መንግስት ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የወያኔ አገዛዝ ግን ዕቅዱና ስራው ሁሉ የኢትዮጵያን ህዝብ ማስጨነቅና ማበሳጨት ነው እንጂ የኢትዮጵያ ህዝብ በሚሰራው ስራ ተደስቶ አያውቅም፤ ለወደፊትም የሚደሰት አይመስልም። ከሰሞኑ ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ በኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ላይ የደረሰው ልክ የሌለው ስቃይና መከራ መላውን የኢትዮጵያ ህዝብ ቀፎው እንደተነካ ንብ ከዳር ዳር ሲያስቆጣ ወያኔና ሞራለ ብልሹ ሹማምንቶቹ ግን ከዚህ ወገኖቻችንን በባዕድ አገር ለከፍተኛ ጥቃት ካጋለጠና ብሄራዊ ውርደት ካከናነበን ክስተት ትርፍ ለማግኘት የፖለቲካ ቁማር እየተጫወቱ ነው።
ኢትዮጵያውያን ሳዑዲ ውስጥ በአሰሪዎቻቸው፤ በመንደር ውስጥ ጎረምሶችና በፖሊስ ከፍተኛ ድብደባ፤ እንግልትና ውርደት ሲደርስባቸው ኤምባሲው በራፍ ላይ “ኤምባሲው ዝግ ነው” የሚል ጽሁፍ በመለጠፍ ይበላችሁ እያለ አፉን ዘግቶ የተመለከተው የወያኔ አገዛዝ ዛሬ የወገን አሳቢና ተቆርቋሪ ለመመሰል የጭቃ ውስጥ እሾኩን ቴዎድሮስ አድሀኖምንና የአገዛዙን የውሸትና የቅጥፈት ቃል አቀባይ ዲና ሙፍቲን በግምባር ቀደምትነት በማሰለፍ የፖለቲካውን ገደል ቁልቁል ተያይዞታል።
ቴዎድሮስ አድሃኖም ቢከፋም ቢለማም የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ነው፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የስራ ሀላፊነት ደግሞ አገሪቱንና ዜጎቿን ከውጭ አገሮች ጋር በሚያገኛኙ ጉዳዮች ላይ ማተኮር ነው እንጂ በአገር ውስጥ የሚሰራው ይህ ነው ተብሎ የሚነገር ስራም ሀላፊነትም የለውም። አንዴ ወዳጅ አንዴ ጠላት እየመሰለ እንደ እስስት መልኩን የሚቀያይረው ቴዎድሮስ አድሀኖም ግን ሳዑዲ ውስጥ ድረስልን ብለው ሲጣሩት ፊቱን ያዞረባቸው ኢትዮጵያውያን አዲስ አበባ ሲመለሱ ያሉበት ቦታ ድረስ በመሄድ እንኳን ደህና መጣችሁ ለማለት ሲሞክር ይታያል። ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ የሚገኙትን የኢትዮጵያ ኤምባሲና ቆንስላ ጽ/ቤቶች ቅርቅር አድርጎ ዘግቶ የወገን ያለህ ብለው የመጡትን ኢትዮጵያውያን እንጃላችሁ ብሎ ፊቱን ያዞረባቸው የአዛኝ ቅቤ አንጓቹ ቴዎድሮስ አድሃኖም እነዚሁኑ እንደ ባዳ ፊቱን ያዞረባቸውን ኢትዮጵያውያን አገር ቤት ሲመጡ “እንኳን ደህና መጣችሁ” ማለቱ የገደለውን ወታደር ለማከም ከሞከረው የናዚ ጀርመን ወታደር ተለይቶ የሚታይ አይደለም። ቴዎድሮስ አድሀኖም እንደ ፈረስ ገርተው ለዚህ ባደረሱት በነመለስ ዜናዊና ስብሐት ነጋ ጭቅላት ሳይሆን በራሱ ጭንቅላት የሚያስብ ሰው ቢሆን ኖሮ የሱ የስራ ድርሻና ሀላፊነት ዜጎቻችን አገር ቤት ከገቡ በኋላ ሳይሆን ሳዑዲ ውስጥ እያሉ ነበር።
ዛሬ ቴዎድሮስ አድሃኖምም ሆነ ዘረኞቹ የወያኔ መሪዎች ከሳዑዲ በሚመለሱት ወገኖቻችን ዙሪያ የሚያደርጉት ልታይ ልታይ የፎቶ እሽቅድምድም ወገኖቻችንን ለመርዳት ሳይሆን ዘረኛ መሪያቸው መለስ ዜናዊ ሲሞት ሳያስቡት በድንገት ከእጃቸው የወጣውን የጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታ መልሰው እጃቸው ለማስገባት ወይም በሚቀጥለው አመት በሚደረገውና ወያኔ ከወያኔ ጋር በሚወዳደርበት ትርጉም የለሽ ምርጫ የፈረደበት ኃ/ማሪያም ደሳለኝን በቴዎድሮስ አድሃኖም ለመተካት ነው። አዎ! ለመተካት … ለመተካካት። ወያኔ መተካካት እያለ አንዱን ጌኛ በሌላ ጌኛ በልቶ የጠገበውን አህያ በተራበ አህያ መተካት ከጀመረ ውሎ አድሯል። የአሁኑም ሩጫቸው ቢጭኑት አልሸከም ቢቀመጡበት አልመች ያላቸውን ኃ/ማረሪያም ደሳለኝን የራሳችን ሰው ብለው በሚጠሩት በቴዎድሮስ አድሃኖም ለመተካት ነው (ኃይለማሪያምማ አሁንስ ቢሆን በቁሙ አልተተካም ብላችሁ ነው … ድፍን አበሻ ውጭ አገርም አገር ውስጥም ሲተራመስ ኃ/ማሪያም አንዲት ቃል አልተነፈሰምኮ)።
ሳዑዲ ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወንድሞቻችን ፓስፖርታቸውን ሲቀሙ፤ ሲደበደቡ፤ሲታሰሩና ሲገደሉ ቴዎድሮስ አድሀኖም የሰጠው ምላሽ ቢኖር የኤምባሲውንና የቆንስላ ጽ/ቤቶችን በር መዝጋት ነበር። አዎ መዝጋት። ልክ ከ1997ቱ ምርጫ በኋላ ከመለስ ዜናዊና ከአግዓዚ ነብሰ ገዳዮች የጥይት እሩምታ ለማምለጥ ወደ ቤተክህነት ጽ/ቤት ግቢ ሸሽተው ለመግባት በሞከሩ ወጣቶችና ህፃናት ላይ አባ ጳውሎስ በሩን እንደዘጉባቸው ዛሬም የአባ ጳውሎስ ታናሽ ወንድም የሆነው ቴዎድሮስ አድሃኖም በባዕድ አገር ውስጥ አድነን ብለው በተጠጉት ወገኖቻችን ላይ የኤምባሲን በር ቀርቅሮባቸዋል።
ለመሆኑ ቴዎድሮስ አድሃኖም በየአመቱ ከ40ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በለጋ ዕድሜያቸው ከወላጆቻቸው ተለይተውና ትምህርታቸውን ትተው ስራ ፍለጋ ወደ አረቡ አለም የሚጎርፉት እሱ ሊነግረን እንደሚፈልገው በአትራፊ ደላላዎች ተታልለው ወይም የአረብ አገር ኑሮ ጥሟቸው ሳይሆን ወያኔ በሚከተለው የዘረኝነት ፖሊሲና የተበላሸ የኤኮኖሚ ስርዐት የተነሳ መሆኑን ያውቅ ይሆን? በተለይ ወጣት ሴቶቻችን በአረቡ አለም የሚደርስባቸውን ውርደትና መከራ እያወቁ በነጋ በጠባ አረብ አገር የሚሄዱት አገራቸው ውስጥ ሰርተው መኖር ስላልቻሉ ከወያኔ ጋር ከመኖር አረብ አገር ሄዶ መሰንበት ይሻላል ብለው ነው አይናቸው እያየ የሞት ወጥመድ ውስጥ የሚገቡት።
ወያኔ በእጥፍ ድርብ አሳደግኩት የሚለው የአለማችን ፈጣኑ ታዳጊ ኤኮኖሚ ለእነዚህ ዜጎች የስራ ዕድል ፈጥሮ ቢሆንና ዜጎች ስራ የሚያገኙት ችሎታቸው ብቻ እየታየ ቢሆን ኖሮ ይህ ዛሬ የምናየው ብሄራዊ ችግርና ውርደት አይኖርም ነበር። ይሉኝታና እፍረት የሚባል ነገር አብሮት ያልተፈጠረው ቴዎድሮስ አድሃኖም የዜጎቻችንን ወደ አረብ አገር መጉረፍ በደላሎችም ሊያሳብብ ሞክሯል። አሱ ለሚከስሳቸው ደላሎች የስራና የንግድ ፈቃድ ሰጥቶ በዜጎች ንግድ እንዲከብሩ መንገዱን ያመቻቸውና የከፈተው የራሱ የቴዎድሮስ ፓርቲ ነው፤ ብዙዎቹ አትራፊ ደላላዎችም የራሱ የቴዎድሮስ ጓደኞች ናቸው። የቴዎድሮስ አድሃኖም ጉድ ብዙ ነው፤ ተዘርዝሮ አያልቅም።
ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ሳዑዲ ውስጥ ሲጋዙና ሲገደሉ ቁጥሩ ተገኗል እያለ በወገኖቻችን ላይ ያፌዝ የነበረው ቴዎድሮስ አድሃኖም ነበር፤ ኢትዮጵያውያን ወገንና ረዳት አለን ብለው ወደ ኤምባሲው በብዛት ሲመጡ ኤምባሲውና ቆስንላ ጽ/ቤቶች በራፍ ላይ “ዝግ ነው” የሚል ጽሁፍ ለጥፎ ወገኖቻችንን ለባዕዳን ጥቃት አሳልፎ የሰጠው ቴዎድሮስ አድሀኖም ነው፤የሳዑዲ መንግስት በአገሩ ውስጥ ወንጀል ሲፈጸም ህጋዊ እርምጃ መውስድ መብቱ ነው ብሎ የወገኖቻችንን መገደልና የሴቶች እህቶቻችንን መደፈር ህጋዊ ለማድረግ የሞከረውም ቴዎድሮስ አድሃኖም ነው። የሚገርመው ይህ ወገኖቻችንን በባዕድ አገር “አይናችሁን ለአፈር” ብሎ በሩን የዘገባቸው ከሃዲ ሰው ነው ዛሬ የወገን አሳቢና ደራሽ መስሎ ቀልዱ እንዳማረለት የመድረክ ላይ ኮሜዲያን እዚህም እዚያም ሽርጉድ የሚለው። ሳዑዲ ውስጥ በወገኖቻችን ላይ ለደረሰው ይህ ነው የማይባል ትልቅ በደልና ጥፋት የኢትዮጵያ ህዝብ በዋናነት ተጠያቂ ከሚያደርጋቸው የወያኔ ባለስልጣኖች ውስጥ ቴዎድሮስ አድሃኖምና ተላላኪው ዲና ሙፍቲ የመጀመሪያዎቹ ናቸው።
ከሰሞኑ ፊቱን እያሳመረ በየደቂቃው ኢቲቪ ላይ መቅረብ የጀመረው ቴዎድሮስ አድሃኖም “ሳዑዲ ውስጥ ለደረሰው ጥፋት መንግስት ተመጣጣኝ እርምጃ ይወስዳል” እያለ ሲዘለብድ ተሰምቷል፤ የሱ ተላላኪ የሆነው ዲና ሙፍቲ ደግሞ “በዜጎች ላይ ምን ግዜም ድርድር የለም” ብሎ ሲናገር ተደምጧል። ይህንን በሁለት ባዶዎች የተነገረ ባዶ ንግግር ያዳመጠ የኢትዮጵያ ህዝብ ግን “ጽድቁ ቀርቶበኝ በወጉ በኮነንከኝ” እያለ የቴዎድሮስንና የዲና ሙፍቲን “ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ” ንግግር ሰምቶ እንዳልሰማ አልፎታል። የሚገርመው ይህ ወገኖቻችንን በክፉ ቀን ወግዱ ብሎ ፊቱን ያዞረባቸው ቴዎድሮስ አድሀኖም ነው ዛሬ የሳዑዲ መንግስት በራሱ ወጪ አዲስ አበባ የሚልካቸውን ዜጎች ዘመድ መስሎ ለመጠየቅ የሚሄደው። ደግሞኮ እስከዛሬ ድረስ አዲሰ አበባ ገብተዋል የሚባሉት በጣት የሚቆጠሩ ሰዎችም ቢሆኑ በተለመደው የወያኔ የዘመድ አሰራር እየተመረጡ የመጡ እንጂ ዜግነታቸው፤ ዕድሜያቸውና የጤንነት ሁኔታቸው እየታየ የተመረጡ ሰዎች አይደሉም።
በአጠቃላይ የተጣለበትን አገራዊ አደራና የተሰጠውን ህዝባዊ ሀላፊነት መወጣት የተሳነውን ቴዎድሮስ አድሀኖምን በየሜድያውና በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ እያሽሞነሞኑ ለማቅረብ የሚደረገው ጥረት እንደ ህፃን ልጅ ሽንት መቀበያ የቆሸሸውን የወያኔ ፊት በቆሻሻ ውኃ ከማጠብ ተለይቶ የሚታይ አይደለም። ወያኔ ከአሳማ አሳማ እየመረጠ ለማሳመርና ለማሽቀርቀር የሚያደርገው ጥረት አሳማውን ወደ ለመደው ወደ ጭቃው ውስጥ ይበልጥ ይስበዋል እንጂ በፍጹም አያሳምረውም፤ ምክንያቱም አሳማ አጌጥነው አላጌጥነው ምን ግዜም አሳማ ነው። የቴዎድሮስ አድሃኖም ነገርም እንደዚሁ ነው ፤ ወያኔ ያሻውን ያክል ቢቀባውና ቢያሳምረው ቴዎድሮስ አድሃኖም ወያኔነቱን አይለቅም! ወያኔ ደግሞ በልቶ የማይጠግብ ታጥቦ የማይነጻ አሳማ ነው።
No comments:
Post a Comment