የሰብኣዊ መብት የሚያስከፍል የሽብር ጥቃት በኢትዮጵያ?

የሰብዓዊ መብት መንግሥት በመልካም ፍቃዱ አይሰጠንም፣ የሰው ልጆች ሆነን ስለተፈጠርን ብቻ የምናገኘውና በቀለም፣ በዘር፣ በሀብት እና በመሳሰሉት ሳንለያይ ያለምንም አድሎ የምንጠቀመው በነጻ በእግዚያብሄር አማሳል ስለተፈጠርን ብቻ የሚኖረን መብት ነው፡፡ መንግሥት መብቱን ባይሰጠንም የመጠበቅ ኃላፊነቱ ግን የሱ፤ የሀገር (የመንግሥት) ኃላፊነት እንጂ የግለሰቡ (የእኛ) ኃላፊነትም አይደለም፡፡ የሰብኣዊ መብትን የመጠበቅ ኃላፊነት የመንግሥት ነው ስንል መብቶቻችን እንዳይገፈፉ በሕግ አግባብ የመጠበቅ፣ መብቶቻችን ሲገፈፉ አግባብ ባለው የፍርድ አካሄድ የማስጠበቅ እና ሕግ የተላለፈውን መቅጣት አለበት እንደ ማለት ነው፡፡ ችግሩ የሰብኣዊ መብቶቻችን የማስጠበቅ ኃላፊነቱ የመንግሥት እንደመሆኑ መብቶቻችንንም ለመጣስ የመጀመሪያው እራሱ መንግሥት ነው፡፡
ይሄም የሥልጣን ፍቅር ያሰከረው፣ ሥልጣን እና/ወይም መሣሪያ ከሕዝብ የሚበልጥ መስሎ የሚታየው መንግሥት ላይ በብዛት ይታያል፡፡ መንግሥት የሰብኣዊ መብቶች ሊጥስ ከሚችልባቸው አጋጣሚዎች ዋነኛው የኅብረሰቡን ጥቅም (Public interest) ለማስጠበቅ የተወሰኑ ግለሰቦች የሰብኣዊ መብት መጣስ ይኖርባታል በሚል ነው፡፡ የኢትዮጵያው የፀረ ሽብር አዋጁም የብዙኃኑን ሠላም ለማስጠበቅ በሚል የግለሰቦችን ሰብኣዊ መብት እየጣሰ መፈፀም ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ነገር ግን የተላየዩ ሰብኣዊ መብቶችን የሚያስጥስ የሽብር አደጋዎች በኢትዮጵያ ውሰጥ የሉም፡፡ ይልቁንም ከአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ በዊኪሊኪስ ድረ ገጽ አማካኝነት ሾልኮ የወጣው መረጃ (Ref. No. 06ADDISABABA2708) ተፈፀሙ ከተባሉት የሽብር ጥቃቶች በጳጉሜ 1 ቀን 1998 ዓ.ም ተፈፀመ የተባለው ሦስት የቦንብ ጥቃት እራሱ የኢትዮጵያ መንግሥት እንደፈፀማቸው እና ኤርትራንና ኦነግን ተጠያቂ እንዳደረገ ይገልጻል፡፡
የሌለን ሽብር መፍጠር ይልሃል ይህ ነው፡፡ ስለዚህ የሽብር ጥቃት በማያሰጋበት እና “አሸባሪ” በሌለባት ኢትዮጵያ የተለያዩ የሰብኣዊ መብቶችን እየገፈፉ የፀረ ሽብር አዋጅን ማስፈፀም ከአደጋ የሚጠብቀው ሕዝቡን ወይስ መንግሥትን? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ በመጀመሪያ የፀረ ሽብር አዋጁ በሕገ መንግሥት ውስጥ ከተካተቱት የሰብኣዊ መብቶች ውስጥ የትኛዎቹን ይጥሳል? የሚለውን መመለስ ያስፈልጋና ጥቂቶቹን እንሆ፡፡
ከፍተኛ ጥንቃቄ (Due Deligence) ለሰላማዊ ሰልፍ
የሠላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ሲታሰብ ንብረቶችን ማጥፋት፣ በፖሊስ ላይ ጥቃት መፈፀም እና የመሳሰሉት ወንጀል ከመሆናቸው ባሻገር ሠላማዊ የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ ይሸረሽሩታል፡፡ ነገር ግን እነዚህ ተግባራት ወንጀል ቢሆኑም ሽብር አይደሉም፡፡ ይልቁንም “ማንኛውንም ሰው ወይም ቡድን የፖለቲካ፣ ሃይማኖታዊ፣ ወይም የአይዲዎሎጂ ዓላማን ለማራመድ በማሰብ በመንግሥት ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር… የሕዝብ አገልግሎት ለከፍተኛ አደጋ ያጋለጠ፣ የያዘ፣ በቁጥጥር ስር ያደረገ፣ ያቋረጠ፣ ወይም ያበላሸ እንደሆነ…” የሽብር ድርጊት እንደተፈፀመ የፀረ ሽብር አዋጁ ይደነግጋል (የፀ.ሽ.አ.አ.3(6)*) ነገር ግን የሕዝብ አገልግሎት ማቋረጥ ኅብረተሰቡን ምን ዓይነት አሳሳቢ አደጋ፤ ለዛውም እንደ ሽብር የሚቆጠር አደጋ ውስጥ እንደሚጥል ግልጽ አይደለም፡፡ ደግሞም የሠላማያዊ ሰልፍ ሲደረግ በመቶዎች፣ በሺሕዎች ወይም በሚሊዮኖች የሚቆጠር ሕዝብ በወጣበት የትራንስፖርት እና የመሳሰሉት የሕዝብ አገልግሎቶች ሊያቋርጥ ይችላል፡፡ የቴሌኮሙኒኪሽን፣ የመብራት ኃይል፣ የውኃና ፍሳሽ ወይም ሌላ የመንግሥት ሠራተኞች ተቃውሞ ኖሯቸው ከሥራ የመቅረት አድማ ቢያደርጉ የሕዝብ አገልግሎት ሊቋረጥ ይችላል፡፡ በዚህ ዓይነት የሠላማዊ ሰልፍ የሚያደርጉት ሆኑ የሥራ መቆም አድማ ያደረጉት የሽብር ድርጊት ፈፀሙ ሊባል ነው? የሠላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት (የሕ.መ.አ.30(1)*) በተዘዋዋሪ ተገፈፈ ማለት ይሄ ነው፡፡ ለዚህም ነው የተለያዩ ባለሙያዎች እና ድርጅቶች አዋጁ የሽብር ድርጊቶችን ሲያብራራ አደናጋሪ (vague) እና ሰፊ (broad) ስለሆነ መሻሻል ይገባዋል እያሉ የሚጮሁት፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሰፊ ክፍተት መተው በፍ/ቤቶች የተለያዩ ትርጉሞች እንዲሰጡት ከማድረጉ ባሻገር የፍትሕ ሚኒስቴር የፈለገውን ሰው እና/ወይም ድርጅት በሽብር ወንጀል ከሶ ችሎት ለመገተር መንገዱን ክፍት ያደረገዋል፡፡
No comments:
Post a Comment