Tuesday, July 9, 2013

ፖለቲካ በፈገግታ

ፖለቲካ በፈገግታ

አንድ በቅርቡ የሰማሁትና ኮፒራይቱ የህዝብ የሆነ ቀልድ ልንገራችሁ! (ጠያቂውም ተጠያቂውም ህዝብ ነው እያልኳችሁ እንደሆነ ይታወቅልኝ) ኢህአዴግ በቀድሞው ጠ/ሚኒስትር ምትክ የሾማቸው አዲሱ ጠ/ ሚኒስትር፣ በአፍሪካ ህብረት 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓል ላይ የአፍሪካ መሪዎች ውስኪና ሻምፓኛቸውን ሲራጩ እሳቸው ግን በራሳቸው የግል ምክንያት ለስላሳ ያዛሉ፡፡ ያዘዙት መጥቶላቸው ሲጠጡ የተመለከተ አንድ ከፍተኛ የኢህአዴግ አመራር ደንግጦ ወደ ጠ/ሚኒስትሩ ጠጋ ይልና “ክቡር ጠ/ሚኒስትር፤ የቀድሞው ጠ/ሚኒስትራችን እኮ ወይን ነበር የሚጠጡት” ይላቸዋል፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ ድንግጥ ብለው “በል ይሄን ውሰድና ወይኑን አስመጣልኝ” ይላሉ – ለስላሳውን በመመለስ፡፡ ወይኑ እንደመጣላቸውም እየመረራቸውም ቢሆን መጎንጨት ይጀምራሉ፡፡ ቀደም ሲል ለስላሳ ይዘው እንደነበረ ያስተዋለ አንድ የአፍሪካ አገር መሪ “ክቡር ጠ/ሚኒስትር ምን ያዙ?” ሲል ይጠይቃቸዋል – ከለስላሳ ወደ ወይን የመሻገራቸውን ሰበብ ለማወቅ በውስጡ ጉጉት ተፈጥሮበት፡፡ ጠ/ሚኒስትሩም በብርሃን ፍጥነት “መለስ የጀመረውን—” ሲሉ ይመልሱለታል፡፡ (የቀልዱ ኮፒራይት የህዝብ መሆኑ እንዳይረሳ በድጋሚ አሳስባለሁ!) ከጀመርኩ አይቀር ሌላ የህዝብ ቀልድ ልጨምራ – አሁንም በኢህአዴግ ዙሪያ ነው ቀልዱ (የህዝብ ፓርቲ ስለሆነ በህዝብ ቀልድ አይቀየምም ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ!) በዘንድሮው የ“ቢግ ብራዘር አፍሪካ” ውድድር ላይ ተሳትፋ “ጉድ ሰራችን” የተባለችው ወጣት ኢትዮጵያዊት “የወሲብ ቅሌት” በፌስቡክ ዋና የአገር አጀንዳ (እናት አገሯን አስደፍራለች እስከመባል መደረሱን ያስታውሷል) የሆነ ሰሞን፣ በመንግስት ደረጃም ለውይይት ቀርቦ ነበር ይላሉ – የቀልዱ ምንጮች፡፡ (ኮፒራይቱ የህዝቡ ነው ማለቴ ይሰመርበት) እናም የአገሪቱ ከፍተኛው የመንግስት ባለሥልጣን የሆኑት ጠ/ ሚኒስትሩ አንጋፋ የኢህአዴግ መሥራችና ሚኒስትር የሆኑ የሥራ ባልደረባቸውን እንዲህ ሲሉ ይጠይቃሉ – “እኔ የምለው የዚች ልጅ ጉዳይ — የአገርን ገፅታ አያበላሽም እንዴ?”
ሚኒስትሩም “ህግመንግስቱን የሚንድ ተግባር እስካልፈፀመች ድረስ የሚያሳስብ ነገር የለውም” በማለት እንዳረጋጓቸው የቀልዱ ምንጮች ያወሳሉ፡፡ ይሄ እንግዲህ ቀልዱ ነው፡፡ ወደ እውነቱ ስንመጣ ግን በ“ቢግ ብራዘር አፍሪካ” ላይ የተሳተፈችውና የወሲብ ቅሌት ፈፅማለች የተባለችው ወጣትና ድርጊቱን በቲቪ የቀጥታ ስርጭት አስተላልፏል የተባለው ጣቢያን ፍርድቤት እንገትራቸዋለን የሚል በወኔ የታጀበ መረጃ ሰምቻለሁ፡፡ እንደሚመስለኝ ምክንያቱ ደግሞ የአገርን ገፅታ ማበላሸታቸው ነው። ለእኔ ግን ከዚህ ይልቅ የአገርን ገፅታ የሚያበላሸው ከኋላቀር የፖለቲካ ባህላችን ጋር ተያይዞ በሚከሰተው የሥልጣን ሽኩቻ ሳቢያ የሚደርሰው የነፃነት አፈናና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይመስለኛል (ተረት ለማድረግ የዛትንበት ድህነታችንም ሳይረሳ!) እናም ጉልበታችንን፣ አቅማችንና ገንዘባችንን በተጨባጭ ለሚጠቅመን ጉዳይ ብናውለው ይሻላል ባይ ነኝ (ለምሳሌ የነፃነትና የሰብዓዊ መብትን ፋይዳ በሚያስገነዝብ ትምህርትና ስልጠና ላይ!)

No comments:

Post a Comment